ቀጥታ፡

በክልሉ 120 ሺህ ተማሪዎች የምገባ መርሐ ግብር ተጠቃሚ ይሆናሉ   

ቦንጋ፤ ሕዳር 13/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በትምህርት ዘመኑ 120 ሺህ የቅድመ አንደኛ ተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ ገለፀ።

የትምህርት ዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ከተጀመሩ ተግባራት መካከል የሚጠቀሰው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም መጠነ ማቋረጥና መቅረትን በመቀነስ ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል ጉልህ ሚና እያበረከተ ነው።  

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትልና የመማር ማስተማር ዘርፍ ኃላፊ ደስታ ገነሜ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በትምህርት ዘመኑ የቅድመ አንደኛና የተለየ ችግር ያለባቸው 120 ሺህ ተማሪዎችን የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ 


 

በእስካሁኑ ሂደት ከ36 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባው ተጠቃሚ መሆናቸውን የጠቀሱት ኃላፊው ምገባ ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶች ፈጥነው ወደዚህ ተግባር እንዲገቡ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የምገባ ፕሮግራሙ በተማሪዎች ውጤት መሻሻል፣ መጠነ ማቋረጥና መቅረት ላይ ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ተግባር እንደሚጠናከር ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የምገባ ፕሮግራም ከጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል በካፋ ዞን የሚገኙት የቦባ ቆጫና የሸታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተጠቃሽ ናቸው።


 

የትምህርት ቤቱ መምህራን፣ ርዕሰ መምህራንና ወላጆች፤ ምገባ መጀመሩ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩና በአግባቡ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡

የሸታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አክሊሉ በትሩ የምገባ ፕሮግራሙ የተማሪውን የትምህርት ተነሳሽነትና የመቅረት ምጣኔ መቀነሱን ገልፀው፣ 136 የቅድመ አንደኛ ተማሪዎች የፕሮግራሙ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።


 

በቀጣይም ህብረተሰቡንና ባለሀብቱን በማሳተፍ ወደ አንደኛ ደረጃ በማሳደግ የትምህርት ውጤታማነትን የማረጋገጥ ስራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል። 

የምገባ ፕሮግራም ከተጀመረ ሶስት ሳምንት ማስቆጠሩን ያነሱት የሸታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት አበባ ገብሬ፤ምገባው ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዲማሩ ማድረጉንና የትምህርት አቀባበላቸውም መቀየሩን ተናግረዋል፡፡


 

በዋቻ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ዩኒት የትምህርት ቤቶች መሻሻል ቡድን መሪ አቶ በየነ በዛብህ፤በከተማ አስተዳደሩ በዚህ ዓመት ሁሉንም የቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን የምገባ ተጠቃሚ ለማድረግ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

በከተማ አስተዳደሩ የሚገኘው የቦባ ቆጫ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ፍቅርተ ታደሰ በበኩላቸው፣ በትምህርት ቤቱ ምገባ መጀመሩ ከዚህ ቀደም ይስተዋል የነበረው የተነሳሽትና የመቅረት ችግር እንዲቀንስ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም