ቀጥታ፡

ጎዴ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተጨማሪ ኃይል እንዲሰጥ የዐቅም ማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 13/2018(ኢዜአ)፡- የጎዴ 230 ኪሎ ቮልት ተሸካሚ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ተጨማሪ ኃይል መስጠት እንዲችል ትራንስፎርመር የማስቀመጥ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

እየተከናወነ ያለው ሥራ 25 ሜጋ ቮልት አምፒየር የመጫን ዐቅም ያለው ተጨማሪ ትራንስፎርመር ተከላ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዚህ ትራንስፎርመርም እስከ 22 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት ድረስ ተጨማሪ ኃይል መጫን እንደሚቻል አስረድተዋል።

ሥራው ሲጠናቀቅም ጎዴን ጨምሮ የአካባቢው ከተሞች ነዋሪዎች እንዲሁም በአካባቢዎቹ ሊመጣ የሚችልን የኢንቨስትመንት ፍሰት ተከትሎ የሚቀርብ የኃይል ፍላጎትን እንደሚመልስ አረጋግጠዋል።

የማከፋፈያ ጣቢያውን 77 ሜጋ ዋት የመጫን ዐቅም ለማሳደግ የሚቀመጠው የትራንስፎርመር ተከላ በአንድ ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል።

በአጠቃላይ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋን ጨምሮ በቀብሪ ደሃር፣ ደጋሃቡር እና ጎዴ ከተሞች ከፍተኛ ኃይል የመሸከም ዐቅም ያላቸው የማከፋፈያ ጣቢያዎች እንዳሉ አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም