ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ አራት ጨዋታዎች ፍጻሜውን ያገኛል። 

ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ምድረገነት ሽሬ ከመቻል በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ምድረገነት ሽሬ በሊጉ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሁለት ጊዜ ሲሸነፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ግቦችን አስተናግዷል። 

ቡድኑ በአምስት ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው መቻል በበኩሉ ከአምስት ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ወጥቷል። ስምንት ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ግቦች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ11 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል። 

በሌላኛው መርሃ ግብር ፋሲል ከነማ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ፋሲል ከነማ በሊጉ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል። አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር ያስተናገደው አንድ ግብ ብቻ ነው። ቡድኑ በ11 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው አምስት ጨዋታዎች ሶስቱን በድል ሲያጠናቅቅ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በጨዋታዎቹ አምስት ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ ስድስት ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

ድሬዳዋ በዘጠኝ ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ምሽት 12 ሰዓት ላይ ባህር ዳር ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።

ባህር ዳር ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች መካከል ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አንድ ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በጨዋታዎቹ አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ አምስት ጎሎችን አስተናግዷል። 

ቡድኑ በስድስት ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ ከአምስት ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ድል ሲቀናው ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር  አንድ ጎል ተቆጥሮበታል። ቡድኑ በ11 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።

ከቀኑ 9 ሰዓት አርባምንጭ ከተማ ከሸገር ከተማ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

አርባምንጭ ከተማ በሶስት ነጥብ 17ኛ፣ ሸገር ከተማ በአምስት ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም