የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀትና አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ተስፋ ያላቸው ታዳጊዎች ወደ እግር ኳሳችን እየመጡ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀትና አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ተስፋ ያላቸው ታዳጊዎች ወደ እግር ኳሳችን እየመጡ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2018(ኢዜአ)፦ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀትና አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ተስፋ ያላቸው ታዳጊዎች ወደ እግር ኳሳችን እየመጡ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ከሶማሊያ ቡድን ጋር 3 ለ 3 አቻ የወጣውን ከ17 ዓመት በታች ቡድን ከጨዋታው በኋላ በአካል ተገኝቼ አበረታትቻለሁ ብለዋል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን እንድታዘጋጅ ያቀረቡትን ይፋዊ ጥያቄ ተከትሎ መንግሥት በየአካባቢው ከትናንሽ እስከ ግዙፍ ስታዲየሞችን እየገነባ ይገኛል ነው ያሉት።
ከመሠረተ ልማት ባሻገር ደግሞ የኢትዮጵያውያንን እግርኳስ ወዳድነት የሚመጥን እና መልካም ስማችንን ከፍ የሚያደርግ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተጀምረዋል ብለዋል።
"የጉዞ 2029 ፕሮጀክት" የሆነው ከ17 ዓመት በታች ቡድናችንም ትልቅ ተስፋ ያለውና የኢትዮጵያ ወጣቶችና ታዳጊዎች ኳስ ጨዋታ እንደሚችሉ፣ እንዲሁም ለአህጉራዊ ዋንጫው ከታች የጀመርነው ዝግጅትም ፍሬ እያፈራ መሆኑን ተመልክተንበታል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
ለቡድኑ እዚህ መድረስ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፣ ለኮቺንግ ስታፍ አባላት፣ ለእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች እና ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አመራሮች ምስጋና ለማቅረብ እፈልጋለሁ ብለዋል።
የታዳጊ ቡድኑ አባላት በስካሁኑ የውድድር ሂደት ላስመዘገባችሁት ወጤት በርቱ ማለት እፈልጋለሁ ሲሉም ገልጸዋል።