ማዕድን ለጥቅል ሀገራዊ ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ስትራቴጂክ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ በስፋት እንዲመረቱ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ማዕድን ለጥቅል ሀገራዊ ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ስትራቴጂክ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ በስፋት እንዲመረቱ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2018(ኢዜአ)፦ ማዕድን ለጥቅል ሀገራዊ ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ስትራቴጂክ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በስፋት ማምረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ ተገኘ(ኢ/ር) ገለፁ።
የማዕድን ሀብቶችን በጥናት ለይቶ ለማውጣትና በጥንቃቄ ለመጠቀም ብቃት ካላቸው ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰራም ሚኒስትሩ ለኢዜአ ተናግረዋል።
በማዕድን ልማት ላይ በተደረጉ ማሻሻያዎች ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት እያሳየ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በሀገር ውስጥ እና በወጪ ገበያ ምርት መጠን ላይ እድገት እየተመዘገበ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ማዕድን ትኩረት ከተሰጣቸው አምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ መሆኑን ጠቁመው የዘርፉን ውጤታማነት የሚያሳልጡ የአሰራር ማሻሻያዎችና ሀብቱን የማስተዋወቅ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
ከጉባ ብስራቶች መካከል የ10 ቢሊየን ዶላር ፕሮጀክቶች የማዕድን ዘርፉ መሆናቸውን በማንሳት፤ ይህም ከለውጡ በፊት የነበረውን ከ100 ሚሊዮን ዶላር የማይበልጡ አነስተኛ ኢንቨስትመንቶችን በከፍተኛ ደረጃ የለወጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የማዕድን ዘርፉ በ2017 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ከተገኘው ገቢ 40 በመቶ ድርሻ እንደነበረው ገልጸው፤ ገቢውን ለማሳደግና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ አጋዥ የሆኑ ስትራቴጂክ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን በመግለጽ፡፡
የማዕድን ሀብቶችን በጥናት ለይቶ ማውጣትና በጥንቃቄ መጠቀም ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፤ መንግስት አቅም ካላቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡