የጋምቤላ፣ የኦሮሚያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች ተጎራባች አካባቢዎች የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን በጋራ አከበሩ - ኢዜአ አማርኛ
የጋምቤላ፣ የኦሮሚያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች ተጎራባች አካባቢዎች የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን በጋራ አከበሩ
ጋምቤላ፤ ህዳር 12/2018(ኢዜአ)፡- የጋምቤላ፣ የኦሮሚያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች ተጎራባች አካባቢዎች 20ኛውን የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን በጋራ አከበሩ።
በጋምቤላ ከተማ በተከበረው በዚሁ በዓል ላይ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ የጋምቤላ፣ የኦሮሚያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች የጋራ እሴቶች ያሏቸው ሕዝቦች ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም በዓሉን በጋራ ማክበራቸው ወንድማማችነትና እህትማማችነትን ይበልጥ ያጠናክራል ሲሉ ገልጸዋል።
የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ መሠረት ማቲዎስ፤ በበኩላቸው፤ ቀኑን ስናከብር እራስን በራስ የማስተዳደር መብትንና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከር በማሰብ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህም የጋምቤላ፣ የኦሮሚያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች ተጎራባች አካባቢዎች የእርስ በርስ ግንኙነትና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ በውይይት መከበሩን ተናግረዋል።
በጋራ መከበሩ የልማት አጋርነትን፣ ወንድማማችነትንና የርስ በርስ ግንኙነትን ይበልጥ እንዲያጠናክር በማሰብ መሆኑን አንስተዋል።
በኦሮሚያ ክልል የኢሉባቡር ዞን ተወካይ ሰለሞን በቀለ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በጋራ መከበር የሶስቱ ክልሎች ተጎራባች አካባቢዎች ሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነትን ይበልጥ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
ቀኑ የባህል እሴቶችን ከማስተዋወቅ ባለፈ የአካባቢውን ልማት በጋራ ለማሳደግ ተጨማሪ አቅም ይሆናል ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት የብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ጌታቸው ኬኔ፤ ቀኑን በጋራ ማክበራችን የልማት ትብብራችንንና አብሮነታችንን የሚያጎለብት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድን ጨምሮ ሌሎቸም ከፍተኛ አመራሮችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት መድረክ ሕገ መንግስቱ የፀደቀበትን ዕለትና የፌዴራሊዝም ስርዓቱን የተመለከተ የመወያያ ጽሁፍ ቀርቦ ምክክር ተደርጓል።
ሀገር አቀፉ 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት በሆሳዕና ከተማ እንደሚከበር ይታወቃል።