የአፍሪካን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት ዓለም አቀፍ ትብብርን በማጠናከር በቁርጠኝነት መስራት ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት ዓለም አቀፍ ትብብርን በማጠናከር በቁርጠኝነት መስራት ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 12/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ዓለም አቀፍ ትብብርን በማጠናከር በቁርጠኝነት መስራት እንደሚያስፈልግ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ገለጸ።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዘጋጅነት የ2025 የአፍሪካ ዘላቂ የልማት ሪፖርት ዋና ዋና ግኝቶችና የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦች ላይ የዌብናር ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩም የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት ወሳኔ ሰጪዎች፣ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የገንዘብ ተቋማት፣ ተመራማሪዎችና የልማት አጋሮች ተሳትፈዋል።
በመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የልማት ዕቅድ ክፍል ኃላፊ ኦዬባንኬ አበጂሪን፤ የምንፈልጋትን አፍሪካ ዕውን ለማድረግ በዘላቂ የልማት ግቦች ላይ በትብብር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአፍሪካ ሀገራት የ2030 ዘላቂ የልማት አጀንዳና የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 አፈፃጸም ሂደትን የሚከታተል የሪፖርት ሥርዓት መኖሩንም ገልጸዋል።
እ.ኤ.አ በ2017 የተጀመረው የአፍሪካ ዘላቂ ልማት ሪፖርት ክትትል ሥርዓትም የአህጉሪቷን ዘላቂና ቁልፍ የልማት ማዕቀፎች አፈፃጸም የሚገመገምበትን መድረክ በማመቻቸት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።
እ.ኤ.አ የ2025 የአፍሪካ ዘላቂ ልማት ሪፖርት መድረክም የአህጉሪቷ ልማት በሳይንስና ማስረጃ የተመሰረቱ የመፍትሔ አፈፃጸሞችን ያመላከተ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሪፖርቱም የአፍሪካ ዕድገት በጤና፣ በሥርዓተ ፆታ እኩልነት፣ በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በውቅያኖስ ጥበቃና ዓለም አቀፍ ሽርክና ጋር በአፍሪካ ሀገራት እ.ኤ.አ የ2030 ዘላቂ የልማት ግብና የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ወሳኝ አካል መሆኑን አስረድተዋል።
የአህጉሪቷን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካትም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የትብብር ሥርዓትን በማጠናከር በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የ2025 የአፍሪካ ዘላቂ ልማት ሪፖርትም ወሳኝ የአፈፃጸም ግኝቶችን በማረም የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችን በሚገባ ለመተግበር አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
በመድረኩም የአህጉሪቷን ዘላቂ የልማት ግቦችና አጀንዳዎች የአፈፃጸም ስኬት ልምድና ተሞክሮ በመለዋወጥ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ለመቅረጽ የሚችል ተግባቦት መፈጠሩን አስገንዝበዋል።
በቀጣይም የአህጉሪቷን የልማት ግቦች ለማሳካትም አዲስ ዓለም የፋይናንስ ድጋፍ ማዕቀፍ አስፈላጊነትን ታሳቢ በማድረግ በትኩረት የሚሰራበት ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።
መድረኩም ብሔራዊና ቀጣናዊ የልማት ስኬት አፈፃጸም የአሰራር ስርዓቶችን በመፈተሽ ዕድሎችን በማስፋት የአህጉሪቷን ዘላቂ የልማት አጀንዳዎ ማሳካት እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል።