የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን ተቋማት ላይ በመተግበር ዘመናዊና ቀልጠፋ የመንግስት አገልግሎት መስጠት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን ተቋማት ላይ በመተግበር ዘመናዊና ቀልጠፋ የመንግስት አገልግሎት መስጠት ይገባል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2018(ኢዜአ)፦ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን በተቋማት ላይ በመተግበር ዘመናዊና ቀልጠፋ የመንግስት አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ(ዶ/ር) የተቋሙን የ2018 በጀት ዓመት የአንደኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻፀም ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው አቅበዋል፡፡
ኮሚሽነሩ በሪፖርታቸው፤ በመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የመንግስትን የማስፈጸም አቅም ታሳቢ ያደረገ ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት የጸደቀውን ፖሊሲ መተግበር የሚያስችል ዕቅድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
ከሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ግቦች መካከል የሰው ሀይል ብቃት በማሻሻል የመንግሥት ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ማቀላጠፍ፣ ለመንግሥት ሰራተኞች ማትጊያና ማበረታቻ ስርዓት መዘርጋት ነው ብለዋል፡፡
የመንግሥት ሰራተኞችን የኑሮ ጫና ለማቃለል ሀገር አቀፍ የደመወዝ ጭማሪ መደረጉን በመጥቀስ፤ ለሀገረ መንግስት ግንባታ የሚያስፈልገውን ሲቪል ሰርቪስ ማፍራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሳውን ቅሬታ ለመፍታት በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዘመናዊ በሆነ መንገድ አገልግሎቶች መሰጠት ተጀምሯል ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት ሁሉን አቀፍ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን ውጤታማ ለማድረግ ወደ ትግበራ የገቡ ተቋማትን አፈጻጸም ለማጠናከር ስለተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡
ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ(ዶ/ር) ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ በፌዴራል ተቋማት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ትግባራ እውን እንዲሆን ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በምክር ቤቱ የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሬ ሌንጮ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ መነሻ ያደረገ ጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደርን ዲጂታል ለማድረግ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች የሚበረታቱ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
በቀጣይም የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን በሁሉም ተቋማት ውጤታማ ለማድረግና ዘርፉን ለማዘመን የተጀመሩ ተግባራት በፍጥነትና በጥራት እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል፡፡
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተመዘገቡ ተጨባጭ ለውጦችን በአግባቡ ማደራጀት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡