የስታርታፕ የፈጠራ ውጤቶች የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማሳለጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የስታርታፕ የፈጠራ ውጤቶች የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማሳለጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2018(ኢዜአ)፦ የስታርታፕ የፈጠራ ውጤቶች የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማሳለጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቦሩ ሻና ገለጹ።
ዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሽፕ ሳምንት የውይይት መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል፡፡
የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቦሩ ሻና በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መንግስት የኢንተርፕርነርሽፕ ምህዳሩን ለማስፋት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡
ዓለም አቀፉ የኢንተርፕርነርሽፕ ሳምንት ስታርታፖች ችግር ፈቺ ከሆኑ የፈጠራ ውጤቶች ልምድ እንዲቀስሙ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ለዘርፉ ውጤታማነት የስታርታፕ አዋጅን ጨምሮ የተለያዩ ህጎችን መውጣታቸውንል፣ አሰራሮች መዘርጋታቸውንና አደረጃጀቶች መፈጠራቸውን ነው የገለጹት።
በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኢንተርፕርነርሽፕ ሥነ ምህዳር በመስፋቱ ችግር ፈቺ የስታርታፕ ውጤቶች መፍለቅ ጀምረዋል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ችግር ፈቺ እና ለገበያ አመቺ የሆኑ ስታርታፖች እየተስፋፉ መምጣታቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ ስታርታፖች በበኩላቸው፤ ዓለም አቀፉ የኢንተርፕርነርሽፕ ሳምንት ስታርታፖች መስራቾችን እንዲተዋወቁ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
የሀናሰን ኬር የሴቶችና የአረጋውያን የንጽህና መጠበቂያ መስራችና ባለቤት ሀናን አህመድ በበኩሏ፤ የኢንተርፕርነርሽፕ ሳምንቱ ስታርታፖች አዳዲስ ነገሮችን እንዲያውቁ ዕድል ይፈጥራል ብላለች፡፡
የእንዝርት ኢንጂነሪንግ ባለቤት ሶፎንያስ ዳዊት ገበያ መርና ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶች ላይ ትኩረት አድርገን እንድንሰራ የሚያበረታታ ነው ብሏል፡፡