ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከቀጣናው አገሮች ጋር በቁርጠኝነት ትሰራለች - ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከቀጣናው አገሮች ጋር በቁርጠኝነት እንደምትሰራ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ (ዶ/ር) ገለጹ።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የግብርና ሚኒስትሮች ወቅቶችን በመከተል በሚደረግ የአርብቶ አደሮችና እንስሳት ድምበር ተሻጋሪ እንቅስቃሴ እና የእንስሳት ሀብት ልማት ላይ ያተኮረ ጉባኤ ተካሂዷል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ አርብቶ አደሩን የሚያጋጥሙ ድንበር ተሻጋሪ ችግሮች በመፍታት በአብሮነት ከቀጣናው አገሮች ጋር ትሰራለች።

ለዚህም የጋራ፣ የተቀናጀ እና ቀጣናዊ መፍትሄዎች መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የእንስሳት ምርታማነትን ለማስቀጠል የግጦሽ መሬት ለመጠቀም እና የተሻለ ህይወት ለመምራት የጋራ ትብብር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ እ.ኤ.አ በ2022 ኢትዮጵያ የፈረመችው የኢጋድ የአርብቶ አደሮችና እንስሳት ድምበር ተሻጋሪ እንቅስቃሴ ፕሮቶኮል ቀጣናዊ መሳሪያ ነው።

ፕሮቶኮሉ በሥርዓት የተደራጀ እንቅስቃሴን በመላው አባል ሀገራት ለማስቻል ወጥነት ያለው፣ በመብቶች ላይ የተመሰረተ እና ወደፊት የሚመለከት ማዕቀፍ መሆኑን አመልክተወል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የግጦሽ መሬቶችን፣ የውሃ ሃብቶችን እና ገበያዎችን በሚጋሩ የአርብቶ አደር ማህበረሰቦች መካከል ሰላማዊ አብሮ መኖርን፣ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን እና የኑሮ ደህንነትን ያበረታታል ብለዋል።

የኢጋድ ምክትል ዋና ጸሓፊ መሀመድ ዋሬ በበኩላቸው፤ ኢጋድ ፕሮቶኮሉ ድንበር ተሻጋሪ አርብቶ አደሮች እና የእንስሳቶቻቸው እንቅስቃሴ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በመላመድ እንደ ግጦሽ እና ውሃ ያሉ አስፈላጊ ሀብቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል ያለመ ነው።

በአርብቶ አደር አካባቢዎች ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እና ለአርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር ማህበረሰቦች ተጨማሪ መተዳደሪያ ሀብት ልማትን ለመደገፍ ያስችላል ተብሏል።

የዓለም እንስሳት ጤና ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ባባ ሶማሬ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ድርጅቱ በኢጋድ የእንስሳት ጤና ደህንነት ለማስጠበቅ ለሚደረገው ተግባር ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል።

የቴክኒካል ድጋፍ፣ የበሽታ ቅድመ ማስጠንቀቅያ መስጠት እና በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ በማድረግ ለዘርፉ እድገት የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግረዋል።

ከጉባኤውም በኋላ የአባል አገራቱ የግብርና ሚኒስትሮች የአርብቶ አደሮችና እንስሳት ድምበር ተሻጋሪ እንቅስቃሴ እና የእንስሳት ሀብት ልማት ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ፕሮቶኮል ተፈራርሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም