ቀጥታ፡

የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን በአግባቡ በመተግበር ሀገራዊ የልማት እቅዶችን ማሳካት ይገባል  

አርባ ምንጭ፤ ህዳር 12/2018(ኢዜአ)፦ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን በተገቢው በመተግበር ሀገራዊ የልማት እቅዶችን ማሳካት እንደሚገባ ተመላከተ።

ዓለም አቀፍ ዘላቂ የወንዶች የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ቀን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዛሬ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።


 

በጤና ሚኒስቴር የስነተዋልዶ ቤተሰብ ዕቅድ፣ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ዘርፍ ባለሙያ ሞቱማ በቀለ በወቅቱ እንዳሉት፣ እንደ ሀገር ዘመናዊ የወሊድ መከላከያ የመጠቀም መጠን አሁን ካለበት 41 በመቶ በ2030 ወደ 54 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ ነው።

ይህን ሀገራዊ ዕቅድ በማሳካት የልማት ዕቅዶችን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የወንዶች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተሳትፎን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ባለፉት ዓመታት በመንግስትና ባለድርሻ አካላት ቅንጅት የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ቢመዘገብም የወንዶች አስተዋጽኦ ክፍተት እንዳለው አስረድተዋል።

የወንዶችን የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተሳትፎን ለማሳደግ ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ይበልጥ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።


 

ወላጆች የልጆቻቸውን ቁጥር በአጋጣሚ ሳይሆን በምርጫ ሊወስኑ እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የማሪስቶፕስ ካንትሪ ዳይሬክተር አበበ ሽብሩ(ዶ/ር) ናቸው።

የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ለዘላቂ የልማት ግቦች መሳካት ያለውን አይነተኛ ሚና ለማጠናከር የወንዶችን ተሳትፎ ማጉላት እንደሚገባ ጠቁመዋል።


 

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የስነ ተዋልዶ ጤናና መብቶች ተቋም ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ድልአየሁ በቀለ በበኩላቸው የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት የጥንዶች ሃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ወንዶች የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት የሴቶች ሀላፊነት ብቻ አድርገው መቁጠራቸው  የአገልግሎቱ ዓላማ በሚፈለገው ልክ እንዳይሳካ ማድረጉን አንስተዋል።


 

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ደስታ ጋልቻ በወንዶች ዘላቂ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ላይ ግንዛቤን ለማስፋት ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ ዘላቂ የወንዶች የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ቀንን ያዘጋጁት ጤና ሚኒስቴር፣ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ ማሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጋራ በመተባበር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም