በአዲስ አበባ ከተማ በተከናወኑ የልማት ተግባራት እመርታዊ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከተማ በተከናወኑ የልማት ተግባራት እመርታዊ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ በተከናወኑ የልማት ተግባራት እመርታዊ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር ገለጹ።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አከባበር አካል የሆነው የሕዝብ ለሕዝብ መድረክ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከክልሎች የተውጣጡ ተወካዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነቶችን ለማዳበርና እየተከናወኑ ያሉ የልማት ውጤቶችን ለመመልከት ዕድል ይሰጣል፡፡
መድረኩ የብልፅግና ራዕዮችን ተጨባጭ ውጤቶች ለመመልከትና ልምድና ተሞክሮ ለመውሰድ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
በለውጡ ዓመታት በከተማዋ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች እመርታዊ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸው፤ ድሉ በመንግስትና ህዝብ የጋራ ጥረት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ለልማት እና ብልጽግና መሳካት በአንድነትና በትብብር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አቶ በርሃኑ ጡሙሮ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአካባቢያቸው ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው ለዚህም ምስጋና ይገባል ነው ያሉት።
ኢፍቱ ተስፋዬ በበኩላቸው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በትብብር መንፈስ በማሳካት ብልጽግናን እውን ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
አቶ ዑዱላ ጌዋ እና እፀገነት ግርማ የተባሉ የመድረኩ ተሳታፊዎችም የወል ትርክትን በማጽናት ለዘላቂ ልማት መትጋት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡