ቀጥታ፡

በደሴ ከተማ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያሳደጉ ነው

ደሴ ሕዳር 12/2018(ኢዜአ) ፦ በደሴ ከተማ ኮሪደር ልማትን ጨምሮ  የተከናወኑ የተለያዩ  የልማት ሥራዎች የሕብረተሰቡ ተጠቃሚነት እያሳደጉ መምጣታቸው  ተገለጸ። 

በከተማው የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ፣ የመንገድ መሰረተ ልማትና ሌሎች የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን የከተማው አስተዳደር አስታውቋል። 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በደሴ ከተማ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን በቅርቡ መጎብኘታቸው የሚታወስ ነው።

በከተማዋ ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎችም የተከናወኑ የልማት ሥራዎችም ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ገልጸዋል። 

የልማት ሥራዎቹ በከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች መጎብኘቱም በቀጣይ ለልማት የሚያደርጉትን አስተዋጾ ለማጠናከር እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።  

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ጋሻው እሸቱ በሰጡት አስተያየት እንዳመለከቱት፣ በከተማው ባልተለመደ ሁኔታ ሰፋፊ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ማደርግ ተችሏል።

የአስፋልት መንገድ፣ የኮሪደር ልማት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ሼዶችና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አንስተዋል።

የልማት ሥራዎቹ ሕዝብን ተጠቃሚ በማድረጋቸው ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የጠየቁት አቶ ጋሻው፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችም የከተማዋን የልማት ሥራዎች መጎብኘታቸው የመንግስት ትኩረትን ያሳያል ብለዋል።

ሌላው ነዋሪ አቶ አለሙ አማረ በበኩላቸው፤ በከተማዋ የተከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ለሕብረተሰቡ የዘመናት የልማት ቁጭት መልስ የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።

ልማት ተነፍጓት በቆየችው ደሴ ከተማ ከሀገራዊ ለውጥ ወዲህ የመንገድ፣ የመናኸሪያ፣ የኮሪደርና ሌሎች የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

በልማት ሥራዎቹም እሳቸውን ጨምሮ ሌሎችም የከተማው ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ በቅርቡ ከፍተኛ አመራሮች የከተማዋን የልማት እንቅስቃሴ መጎብኘታቸው የሕዝብን የልማት ተሳትፎ አነሳስቷል ብለዋል።

በከተማችን እየተካሄደ ያለው ልማትና የከፍተኛ አመራሮች ጉብኝት መንግስት ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሰጠውን ትኩረት ያሳያል ያሉት ደግሞ ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ትግስት ታደሰ ናቸው።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ እንደገለጹት፤ በከተማው ለሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በተሰጠው ትኩረት ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

በሕብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ ጭምር የተጠናቀቁ የጤና፣ የትምህርት፣ የመንገድና መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት በመብቃታቸው ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ሆኗል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ በጥራት ተገንብተው እንዲጠናቀቁ ተገቢ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም