ቀጥታ፡

ለሃዋሳ ከተማ ልማት ግብርን በታማኝነት መክፈልን እንቀጥላለን - ግብር ከፋዮች

ሀዋሳ፤ ህዳር 12/2018 (ኢዜአ)፦ ግብርን በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል ለሀዋሳ ከተማ ልማት መጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የከተማዋ ግብር ከፋዮች ተናገሩ። 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ግብር ከፋዮች እንዳሉት የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የድርሻቸውን እየተወጡ ናቸው።

ከከተማዋ ግብር ከፋዮች መካከል የቴዲ ማተሚያ ድርጅት ባለቤት አቶ ዘመን ዘውዴ ባለፉት ሁለት ዓመታት ታማኝ ግብር ከፋይ በመሆን ተሸላሚ እንደነበሩ አስታውሰው፣ በቀጣይም ይህንን የዜግነት ሀላፊነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በከተማዋ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ሥራዎቸ ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት ግብር ከፋዩ፣ ግብሬን በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል የከተማዋን እድገት ለማፋጠን በሚሰሩ የልማት ሥራዎች ተሳትፎዬን አጠናክራለሁ ብለዋል፡፡

ለአሥር ዓመት በተከታታይ በታማኝ ግብር ከፋይነት ዕውቅና እንደተሰጣቸው የተናገሩት ደግሞ በሕንፃ መሳሪያ፣ በሞል እና በዱቄት ፋብሪካ ሥራ የተሰማራው የአድማስ ተስፋ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አስቻለው አድማሱ ናቸው።

ሀዋሳ ከተማ በየጊዜው ልማትና እድገቷ እየተፋጠነ ያለው በሚከፈል ግብር በመሆኑ ኩራት ይሰማኛል ያሉት አቶ አስቻለው፣ በአሁኑ ወቅትም በከተማ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የህዝብን ተሳትፎ ይፈልጋሉ ብለዋል።

የኮሪደር ልማትን ጨምሮ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ለማስቀጠል የሚያደርጉትን የልማት ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩም ገልጸዋል።

በኮንስትራክሽንና በሕንፃ መሳሪያ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ሃይማኖት ተዘራ በበኩላቸው እንደተናገሩት በየዓመቱ የሚጠበቅባቸውን ግብር በአግባቡ እየከፈልኩ ነው፡፡

ግብርን በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል የከተማዋ ልማት በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንደሚያጠናክሩ ጠቁመዋል፡፡

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልኩ ማርቆስ በከተማዋ ግብርን በታማኝነት የመክፈል ልምድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

ይሁንና ገቢን አሟጦ ከመሰብሰብ አኳያ አሁንም የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

"ባለፈው በጀት ዓመት 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 93 በመቶ ማሳካት ችለናል" ያሉት አቶ መልኩ፣ ዘንድሮም  ከ6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደስራ ተገብቷል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እንደተቻለም ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም