ቀጥታ፡

ዜጎች እምቅ አቅማቸውን በመጠቀም ውጤታማ እንዲሆኑ በክህሎት ልማት ላይ ትኩረት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2018(ኢዜአ)፦ ዜጎች እምቅ አቅማቸውን ከአካባቢያቸው ጸጋዎች ጋር አሰናስለው ውጤታማ እንዲሆኑ በክህሎት ልማት ላይ ትኩረት መደረጉን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለጹ፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት በጋራ ባዘጋጁት የልምድ ልውውጥ መድረክ ኢንተርፕርነሮች ለተለያዩ ወጣቶች ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ፈተናን ወደ እድል የሚቀይር ትውልድ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ይህን ለማሳካት ደግሞ በክህሎት ልማት እና ኢንተርፕርነርሺፕ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን ለመመለስ የመደመር መንግሥት ያስቀመጣቸውን የፈጠራ፣ የፍጥነትና የዝላይ መርሆዎች ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

መንግስት የፈጠራ ምህዳሩን ምቹ ለማድረግ ያከናወናቸው የሪፎርም ማሻሻያዎች የክህሎት ልማትን ለማሳደግና የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ተደራሽ እንዲሆኑ አስችሏል ብለዋል፡፡

በዓለም አቀፍ የስራ ፈጠራ ውድድር አሸናፊ የሆኑ የፈጠራ ስራዎች ወደ ቢዝነስ እንዲቀየሩ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡

የፈጠራ ስራዎቹ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡

ኢትዮጵያ በኢንተርፕርነሽፕ ሁነቶች ዝግጅት በዓለም የቀዳሚነትን ስፍራ መያዟ ለተሰጠው ትኩረት ማሳየ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዜጎች እምቅ አቅማቸውን ከአካባቢያዊ ጸጋ ጋር አሰናስለው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚከናወኑ የክህሎት ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

የኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲቱዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቦሩ ሻና በበኩላቸው፤ ስልጠና መስጠት፣ ማማከርና የስራ ፈጠራ ከኢንስቲቱዩቱ አብይ ተልዕኮዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ የፈጠራ ባህልን በማሳደግና ለችግሮች የማይበገር ትውልድ በመገንባት ረገድ የራሱን አሻራ ማሳረፉን ጠቅሰዋል፡፡

የጊዜ ካምፓኒ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ጊዜሽወርቅ ተሰማ፤ ስራ ፈጣሪ ለመሆን ራስን ማብቃትና የትኛውንም አይነት ስራ ለመስራት ዝግጁ መሆንን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች በተሰማሩበት የስራ መስክ ስኬታማ ለመሆን ግብ ማስቀመጥ እና ፈተናዎችን በትዕግስት መሻገር እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት፡፡

ወጣት አለም ጌታሁን ከልምድ ልውውጡ በስራ አለም ሁሉም ነገር ምቹ አለመሆኑን መረዳቷን ገልጻ ጽናት ካለ የማይታለፍ ፈተና እንደሌለ ተምሬበታለሁ ብላለች፡፡

ተግዳሮቶችን ወደ እድል ለመቀየር ሁሌም ራስን ማብቃት እንደሚገባ ከቀደሙት ኢንተርፕርነሮች ልምድ ወስጃለሁ ያለው ወጣት ይድነቃቸው አባይነህ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም