በክልሉ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የቡና መጠን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የቡና መጠን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል
ሚዛን አማን ፤ሕዳር 12/2018(ኢዜአ)፡-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የቡና ጥራትን በማስጠበቅና ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን መጠን ከፍ በማድርግ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
በክልሉ ከ71 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።
የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አሥራት መኩሪያ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ የቡና ጥራትን ለማስጠበቅና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ መጠንን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል።
ህጋዊ የቡና ግብይት ስርዓትን በማጠናከር ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ዘንድሮ ከ71 ሺህ ቶን በላይ የታጠበና ያልታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን ገልጸው፣ ዕቅዱን ለማሳካት የቡና ጥራትና ቁጥጥር ግብረ ኃይል ተደራጅቶ ወደሥራ ገብቷል ብለዋል።
ያልቀላ ቡናን መልቀም፣ ቡናን መሬት ላይ ማድረቅና የደረቀ ቡናን በምቹ መጋዘን አለማስቀመጥ ለቡና ጥራት መጓደል ምክንያት መሆናቸውን ገልጸው፣ እነዚህን ችግሮች ለመከላከል የግንዛቤ ማሳደጊያ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
የቡና ምርታማነት ከአምናው የተሻለ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ከ100 ሺህ ቶን በላይ ቀይ እሸት ቡና ወደ ታጠበ ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪ ለማስገባት የታቀደውን ለማሳካት በተደረገ ጥረትም እስካሁን ድረስ ከ47 ሺህ ቶን በላይ ለማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።
የእሸት ቡና ግብይት በተዘጋጁ የግብይት ማዕከላት ብቻ እንዲከናወን መደረጉን ገልጸው፣ ጥራቱን ያልጠበቀ ቡና ወደ እሸት ቡና መፈልፈያ ኢንዱስትሪ እንዳይገባ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።
በቤንች ሸኮ ዞን ሸኮ ወረዳ በእሸት ቡና ኢንዱስትሪ የተሰማሩት አቶ መሐመድ አሊ በግብርና ባለሙያዎች የተሰጡ የጥራት ማስጠበቂያ መንገዶችን ተከትለው እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ጥራት የሌለው ቡና ሲደርቅ ከደረጃ በታች በመሆን ጉዳት እንደሚያስከትል ጠቅሰው፣ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማዘጋጀት ቡናን ፈትሸው እየገዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሸካ ዞን የአንድራቻ ወረዳ ነዋሪ አቶ ዓለሙ ደይኒ ፤በጓሯቸው በሁለት ሄክታር መሬት ማሳ ቡና በማልማት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ዘንድሮም ከግብርና ባለሙያዎች ያገኙትን የቡና ጥራት መጠበቂያ ምክር ተከትለው ያለሙትን ቡና ቀይ ቀዩን ብቻ በመልቀም እስካሁን ድረስ 8 ኩንታል እሸት ቡና ለኢንዱስትሪ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
ዘንድሮ ከአምናው የተሻለ የቡና ምርት በመኖሩ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆን ተስፋ ማድረጉን የተናገረው አርሶ አደር ተካልኝ ተሰማ ነው።
እሸት ቡናን በጥራት በመልቀም በአቅራቢያው ከሚገኝ የግብይት ማዕከል ጋር ሕጋዊ በሆነ መንገድ እየተገበያየ መሆኑን አክሏል።
የባለስልጣኑ መረጃ እንደሚያሳየው ከክልሉ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ4 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል።
በ2017 የበጀት ዓመት ከ48 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡም ታውቋል።