ቀጥታ፡

ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግ የዲጂታል እውቀት አግኝተናል-ሰልጣኞች

መቀሌ፤ሕዳር 12/2018(ኢዜአ)፡- የኮደርስ ስልጠና መውሰዳችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግ የዲጂታል እውቀት እንድናገኝ አስችሎናል ሲሉ በመቀሌ የኮደርስ ስልጠና የወሰዱ ወጣቶችና ባለሙያዎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቩን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት “የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ” መርሐ ግብር በማደግ ላይ ባለው ዲጂታል ኢኮኖሚ ከባቢ የመጪው ትውልድ ኢትዮጵያዊያንን ለማብቃት ታልሞ የተጀመረ መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል።

የኮደርስ ስልጠናው ዓላማም በእውቀት የዳበረ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ትውልድ ማፍራት መሆኑን በማንሳት ወጣቶች የስልጠናው እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስገንዘባቸው ይታወቃል።

በዚህም መሰረት በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም ወጣቶች የኮደርስ ስልጠና በመውሰድ የእድሉ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።


 

የስልጠናው ተጠቃሚ ከሆኑት መካከልም ወጣት ገነት ጨርቆስ እና ወጣት ሙለይ ኃይሉ ፤ የኮደርስ ስልጠና መውሰዳችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግ የዲጂታል እውቀት እንድናገኝ አስችሎናል ብለዋል።


 

የኮደርስ ስልጠናውን ከወሰዱት የመንግስት ሰራተኞች መካከል አቶ ሰሎሞን ፀጋይ እና ፍሰሃ ነጋ (ኢንጂነር) የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ለሁላችንም የመጣ ነፃ እድል በመሆኑ በመሰልጠን እውቀት አካብተንበታል ብለዋል።


 

ከራስ እውቀትም ባለፈ ለተገልጋዩ ህብረተሰብም በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለመስጠት ሥልጠናው እጅግ ጠቃሚ መሆኑንም አንስተዋል።


 

በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የዲጂታል አቅም ግንባታ ዳይሬክተር አቶ እያሱ ተካ፤ ለወጣቶች የዲጅታል ክህሎት ስልጠና መሰጠቱ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።


 

በዚህም መሰረት በትግራይ ክልል እስካሁን ከ30 ሺህ የሚበልጡ ዜጎች የኮደርስ ስልጠና መውሰዳቸውን ጠቁመው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል። 

በቀጣይ ሶስት ዓመታትም ከ200 ሺህ የሚበልጡ ከ12ኛ ክፍል በላይ የሆኑ ተማሪዎችን የስልጠናው ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል። 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም