ቀጥታ፡

ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ 

ጂንካ፤ሕዳር 12/2018(ኢዜአ)፡- የማርበርግ ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ቫይረሱ ለተገኘባቸው ህሙማን የተለዩ ማዕከላት ምልከታ አድርገዋል። 

በዚህ ወቅትም ሚኒስትሯ እንደገለፁት፤ ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ።


 

በአሁኑ ሰአት ሦስት በማርበርግ ቫይረስ የተያዙ ህሙማን ብቻ እንዳሉና ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ቫይረሱ እንዳይዛመት ህብረተሰቡ የመከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ እንዲያደርግም አሳስበዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፤ የማርበርግ ቫይረስ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳያስከትል ሁሉንም ተቋማት ያሳተፈ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

ህብረተሰቡ በጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር በአግባቡ በመተግበር የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚደረገውን ስራ እንዲያግዝ አቶ ጥላሁን ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ በበኩላቸው ፤የማርበርግ ቫይረስን ለመከላከል ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ለህብረተሰቡም የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የጤና ተቋማትን በህክምና ቁሳቁሶች በማደራጀት የመከላከሉን ስራ ውጤታማ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስቴር ቫይረሱን ለመከላከል የሚያግዙ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የምርመራና የህክምና መስጫ ቁሳቁስ ድጋፍ ለሆስፒታሉ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም