ቀጥታ፡

በመገንባት ላይ የሚገኙት አዳዲስ ሆስፒታሎች ከተማዋን የህክምና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው

አዲስ አበባ፤ሕዳር 12/2018(ኢዜአ)፡-በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ኮልፌ ቀራንዮ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች በመገንባት ላይ የሚገኙት አዳዲስ ሆስፒታሎች ከተማዋን የህክምና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ለተያዘው ግብ ስኬት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

ከንቲባ አዳነች የሆስፒታሎቹን የግንባታ ሂደት የጎበኙ ሲሆን ግንባታቸው በመጠናቀቅ ሂደት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጤና አገልግሎቱን ፍትሃዊና ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን ጥራቱን የጠበቀ እና ዘመኑን የዋጀ የጤና አገልግሎትን በመስጠት ከተማዋን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ግብ ጥሎ እየሰራ ይገኛል፡፡


 

የከተማ አስተዳደሩ ግዙፍ እና ዘመናዊ የሆኑ ሆስፒታሎችን በሶስት ክፍለ ከተሞች እያስገነባ ሲሆን የነዚህን ሆስፒታሎች የግንባታ ሂደት የጎበኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ አዳዲሶቹ ሆስፒታሎች ከተማዋን የህክምና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ለተያዘው ግብ ስኬት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል፡፡

አዳዲሶቹ ሆስፒታሎች ከግዝፈታቸው በላይ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ ትኩረት መደረጉን የተናገሩት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከከተማ አልፈው እንደሀገርም ትልቅ ትርጉም ያላቸው ናቸው ብለዋል፡፡

ሆስፒታሎቹ ከሀገር አልፈው እንደምስራቅ አፍሪካም የልህቀት ማዕክል እንዲሆኑ ታስበው መገንባታቸውን የተናገሩት ከንቲባዋ ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡


 

የከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ የህክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ከማስፋት በዘለለ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ የውጭ ዜጎች እና ዲፕሎማቶች አገልግሎቱን በሀገር ውስጥ እንዲያገኙ ማድረግን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ ያስታወቁት፡፡

አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በመንግስት ከሚከናወነው የጤና ዘርፍ ኢንቨስትመንት ጎን ለጎን የግሉ ዘርፍም ሰፋፊ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም