የብሔሮች፤ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር አብሮነትና ወንድማማችነት እንዲጠናከር መሰረት ጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
የብሔሮች፤ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር አብሮነትና ወንድማማችነት እንዲጠናከር መሰረት ጥሏል
አዲስ አበባ፤ሕዳር 12/2018(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር አብሮነትና ወንድማማችነት እንዲጠናከር መሰረት መጣሉን የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ መሐመድአሚን በድሩ ገለጹ።
20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ የባለሙያዎች ቡድን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቀቤና ልዩ ወረዳ ጉብኝት እያደረገ ይገኛል፡፡
ቡድኑ የቀቤና ብሔረሰብ የባህል ማዕከልና ሙዚየም እና የማህበረሰቡ የዳኝነት ስርዓት ጎብኝቷል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ መሐመድአሚን በድሩ በዚሁ ወቅት፤ የብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የህዝቡን አንድነት በማጠናከር የመቻቻል እና የመከባበር እሴቶች እንዲጎለብቱ መሰረት መጣሉን ተናግረዋል።
የበዓሉ መከበር ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ያላቸውን ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የሆኑ ቅርሶችን እንዲሁም ያሉ ፀጋዎችን እና የባህል እሴቶችን ለማስተዋወቅ ጉልህ አበርክቶ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
የጋራ የሆኑ ትርክቶችን አጉልቶ በማውጣት ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልፅግና ጉልህ አበርክቶ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ዘንድሮ በክልሉ የሚከበረው የዘንድሮው የብሔር፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ያሉ ፀጋዎችን እና እሴቶችን በአግባቡ ለማስተዋወቅ እድል የፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።
ልዩ ወረዳው በዓሉን ለማክበር ከብዙ አካባቢዎች ወደ ክልሉ የሚመጡ እንግዶች መውጫና መግቢያ በመሆኑ ወንድማማችነትን በሚያጎለብት መንገድ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አንስተዋል።
20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት "ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ ህዳር 29 ቀን 2018 በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሆሳዕና ከተማ ይከበራል።