ቀጥታ፡

ሶስተኛው የኢጋድ የሚዲያ አዋርድ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ሕዳር 12/2018(ኢዜአ)፡-ሶስተኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የሚዲያ አዋርድ ኅዳር 20 እና 21/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

በኢትዮጵያ መንግሥትና ኢጋድ ትብብር በተዘጋጀው ሽልማት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የተሻለ የይዘት ስራ ለሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ሙያተኞች የሚበረከት መሆኑ ተገልጿል።

ሶስተኛውን የኢጋድ የሚዲያ አዋርድ የዝግጅት ሂደት አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው እና በኢትዮጵያ ኢጋድ ተጠሪ አበባው ቢሆነኝ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት እየተተገበረ የሚገኘው  የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ቀጣናዊ ልማት አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል። 

በዚህም ብራዚል ቤለም በተካሄደው የዓለም የአየር ንብረት (COP-30) ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት (COP-32) ጉባኤ ለማስተናገድ መመረጧን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ሶስተኛውን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የሚዲያ አዋርድ ማስተናገዷም ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ስኬቶች ዕውቅና የሚሰጥ ነው ብለዋል።

በሚዲያ አዋርድ ሽልማት ውድድሩ ላይ በርካታ ኢጋድ አባል ሀገራት የመገናኛ ብዙሃን ሙያተኞች እንደሚሳተፉም አስታውቀዋል።

የሽልማት ሥነ-ስርዓቱ በአዲስ አበባ መካሄዱም በፐብሊክ ዲፕሎማሲ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የኢጋድ  ተጠሪ አበባው ቢሆነኝ በበኩላቸው፤ ውድድሩ በቴሌቪዥን፣ሬዲዮ፣ህትመት፣ዲጂታል ሚዲያ እና ሴቶች ዘርፍን ጨምሮ በስምንት ዘርፎች እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

400 የሚሆኑ የኢጋድ አባል ሀገራት ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን ማስገባታቸውን ጠቁመው፤ ከዚህ ውስጥ 94  የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ሽልማቱ በቀጣናው ገንቢ ሚና ያለው ጋዜጠኝነት እንዲጎለብት አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም