ቀጥታ፡

ቀኑ ሕብረብሔራዊ አንድነትን በማጎልበት ለሀገር ብልፅግና ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው 

አዲስ አበባ፤ሕዳር 12/2018(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሕብረብሔራዊ አንድነትን በማጎልበት ለሀገር ብልፅግና መረጋገጥ አይተኬ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ቡዜና አልከድር ገለጹ።

‎20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ህዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ ከተማ አቀፍ የህዝብ ለህዝብ መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

‎በመድረኩ ከተለያዩ ክልሎች የተወጣጡ የብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች፣ የሀይማኖት አባቶች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

አፈጉባኤ ቡዜና አልከድር በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፣ ይህ ቀን የእርስ በርስ ግንኙነቶችን ከፍ ለማድረግና ለመተዋወቅ፣ በሀገር ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ውጤቶችን ለመመልከት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።

የብልፅግና ራዕዮችን ተጨባጭ ውጤት ለመመልከትና ልምዶችን ለመለዋወጥ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መድረኩ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።


 

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሀገሪቱ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች እመርታዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

ድህነትንና ልመናን በማስቀረት በምግብ ራስን ለመቻል የተደረጉ ጥረቶች ለምግብ ሉዓላዊነት መሠረት እንደጣሉ ገልጸዋል።

በተስፋ በለመለመበት በዚህ ዓመት ቀኑን በአዲስ አበባ በጋራ ማክበር ድሎችን በማሰብ ደስታን ከመጋራት በተጨማሪ ቀጣይ ተስፋዎችን ለመጨበጥና ፈተና የሚሆኑ ጉዳዮችን በብልሃት ለመሻገር ቃል ለመግባት ጭምር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

አፈጉባኤዋ፤ ልማት የጋራ ጥረትን እንደሚፈልግ አስገንዝበው፤ በመንግስት ጥረት ብቻ ሳይሆን በሕዝቦች ተሳትፎ ጭምር እንደሚረጋገጥ ጠቁመዋል።

ለሰላም ግንባታና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ዜጋ በጎ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም