ቀጥታ፡

በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ልደታ ክፍለ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ አዲስ አበባ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ይጫወታሉ 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 12/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ፍጻሜውን ያገኛል። 

ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ልደታ ክፍለ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ በኢትዮጵያ ንግድ ሜዳ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ልደታ ክፍለ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች መካከል ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሶስት ጊዜ ሲሸነፍ ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ግቦችን አስተናግዷል።

ቡድኑ በአምስት ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚዋ ሃዋሳ ከተማ በውድድር ዓመቱ እስከ አሁን ባከናወናቸው ስድስት ጨዋታዎች በአራቱ ድል ሲቀናው ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። 11 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ስድስት ግቦች ተቆጥረውበታል።

ሃዋሳ ከተማ በ12 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  ጨዋታው ሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው። 

በሌላኛው መርሃ ግብር አዲስ አበባ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ይጫወታሉ። 

አዲስ አበባ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በአምስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በጨዋታዎቹ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር 13 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ቡድኑ በሶስት ነጥብ የመጨረሻውን 14ኛ ደረጃን ይዟል።

አርባምንጭ ከተማ በውድድር ዓመቱ ካካሄዳቸው ስድስት ጨዋታዎች መካከል ያሸነፈው በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነው። አራት ጊዜ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይቷል። 

አርባምንጭ ከተማ በአራት ነጥብ 13ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።  

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሁለተኛ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም