የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሰባተኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሰባተኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሰባተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።’
ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀዲያ ሆሳዕና በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በውድድር ዓመቱ እስከ አሁን ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች አራቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለት ግቦችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በ12 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ ባከናወናቸው አምስት ጨዋታዎች አላሸነፈም። ሁለት ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ አቻ ተለያይቷል። ሶስት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ስድስት ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ሀዲያ ሆሳዕና በሶስት ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ በድል ጉዞ ለመቀጠል፣ ሀዲያ ሆሳዕና በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን ለማሳካት የሚያደርጉት ነው።
በተያያዘም በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮጵያ መድን ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች መካከል ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሶስት ጊዜ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል። ቡናማዎቹ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አራት ግቦችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በአራት ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን ካካሄዳቸው አራት ጨዋታዎች በአንዱ ድል ሲቀናው በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል። ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ሁለት ግቦች ተቆጥረውበታል።
መድን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በአምስት ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌሎች መርሃ ግብሮች ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 10 በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።