ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የምድብ ሶስተኛ ጨዋታዋን ከሶማሊያ ጋር ታደርጋለች

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 12/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን 16ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣሪያ ጨዋታውን ከሶማሊያ ጋር ያከናውናል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ይካሄዳል።

አዘጋጇ ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ያደረገቻቸውን ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ በስድስት ነጥብ ምድቡን እየመራች ነው።

ቡድኑ በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር አንድ ግብ አስተናግዷል።

ታዳጊ ቡድኑ በጨዋታዎቹ ላይ የወሰደው ብልጫ እና ያሳየው እንቅስቃሴ ከእግር ኳስ ቤተሰቡ አድናቆት እንዲያገኝ አስችሎታል።

ተጋጣሚዋ ሶማሊያ በምድቡ ባደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች አቻ ወጥታለች። በሁለት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ሶስት ግቦችን ስታስቆጥር በተመሳሳይ ሶስት ጎሎች ተቆጥረውባታል።

ኢትዮጵያ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈች አንድ ጨዋታ እየቀራት ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፏን ታረጋግጣለች።

በምድብ አንድ ሌላኛው መርሃ ግብር ኬንያ ከሩዋንዳ ከቀኑ 7 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ኬንያ በአንድ ነጥብ ሶስተኛ፣ ሩዋንዳ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አምስተኛ ደረጃ ይዛለች።

በተያያዘም በምድብ ሁለት ዩጋንዳ ከታንዛንያ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

ታንዛንያ እና ዩጋንዳ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ሁለቱ ሀገራት በጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ጨዋታውን ያሸነፈው ሀገር ለግማሽ ፍጻሜ ማለፉን ያረጋግጣል።

በዚሁ ዕለት በምድብ ሁለት ጅቡቲ ከብሩንዲ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ብሩንዲ እና ጅቡቲ ያለ ምንም ነጥብ በግብ እዳ ተበላልጠው ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ዛሬ ሰባተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም