ቴሌብር የፋይናንስ ተደራሽነት እና አካታችነትን ለማስፋት አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
ቴሌብር የፋይናንስ ተደራሽነት እና አካታችነትን ለማስፋት አስችሏል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ቴሌብር ተጠቃሚዎች በቀላሉ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የፋይናንስ ተደራሽነትና አካታችነትን ለማስፋት ማስቻሉን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።
ኢትዮ ቴሌኮም ከአዋሽ ባንክ ጋር በመተባበር "ጥላ" የተሰኘ አዲስ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት በቴሌብር አማካኝነት አስጀምሯል።
ይህ ትብብር የሀገሪቱን የፋይናንስ አካታችነት ለማስፋት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኢትዮ ቴሌኮም የሀገሪቷን ዲጂታል ኢትዮጵያ ራዕይ እውን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።
ቴሌብርን በመጠቀም በቀላሉ የፋይናንስ አገልግሎት ማግኘት መቻሉን አመልክተው፤ ይህም ለተጠቃሚዎቹ ምቹ፣ ፈጣን እና ደህንነቱ የተጠበቀ የፋይናንስ ተደራሽነት እንዲሰፋ ማድረጉን አንስተዋል።
ቴሌብር የቴክኖሎጂ አቅምን ከባንክ ተቋማት የፋይናንስ ልምድ ጋር የተጣመረበት መሆኑን ጠቅሰው፤ የፋይናንስ አገልግሎትን ወደ ህብረተሰቡ በስፋት እንዲደርስ እያደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ከአዋሽ ባንክ ጋር የተደረገው አጋርነትም ሁለቱ ተቋማት የየራሳቸውን ጥንካሬ ለሀገራዊ ልማት ለማዋጣት እንደሚያስችላቸው ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አስረድተዋል።
"ጥላ" ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ምቹ፣ ፈጣን እና ደህንነቱ የተጠበቀ የፋይናንስ አገልግሎት የበለጠ ለማስፋት እንደሚረዳ ተናግረዋል።
የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፀሀይ ሽፈራው በበኩላቸው፤ "ጥላ" የባንኩን የዲጂታል ለውጥ ለማፋጠን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በቴሌብር በኩል የሚቀርቡት እንደ ማይክሮ ብድር (Micro Credit)፣ የሞባይል ቁጠባ (Mobile Saving) አገልግሎቶች ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው እና አነስተኛ ንግድ ለሚሰሩ ትልቅ ዕድል ይፈጥራሉ ብለዋል።
በቀጣይም ሁለቱ ተቋማት ተጨማሪ አዳዲስ እና ፈጠራ ያላቸው የፋይናንስ አገልግሎቶችን በማጠናከር እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
"ጥላ" የፋይናንስ ዲጂታል አገልግሎት የቁጠባ፣ የግለሰብ ብድር፣ ለአነሰተኛ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ብድር እና የዲቫይስ ፋይናንስ አገልግሎቶች በአንድ ጥላ ስር ለመስጠት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።