የኩላሊት በሽታን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኩላሊት በሽታን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ የኩላሊት በሽታን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጤና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ስር የሰደደ ኩላሊት በሽታን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል መርሃ ግብር አስጀምሯል።
ሚኒስቴሩ መርሃ ግብሩን ያስጀመረው ከፖፕሌሽን ሰርቪስ ኢንተርናሽናል (ፒ ኤስ አይ ) እና አስትራዜኒካ ከተሰኙ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሲሆን ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት እንደሚተገበር ተገልጿል።
መርሃ ግብሩ በጤና ጣቢያዎችና መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ስር ለሰደደ ኩላሊት በሽታ አጋላጭ የሆኑ ግፊት እና ስኳር በሽታዎችን ምርመራ በማድረግ መለየት እና ህክምና የሚሰጥበት ሥርዓት ያካተተ ነው።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንዳሉት፤በኢትዮጵያ ስር የሰደደ ኩላሊት ታማሚዎች ቁጥር ከ6 በመቶ በላይ ነው።
ለዚህ ደግሞ ዋነኛ መንስኤ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የደም ግፊትና ስኳር በሽታ እንደሚገኙበት ጠቁመው መሰል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለዚህም ሚኒስቴሩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ አውጥቶ እየተገበረ መሆኑን ጠቁመው ዜጎች ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አጋላጭ ከሆኑ የአኗኗር ዘይቤዎች ራሳቸውን እንዲጠበቁ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
አካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ስብ የበዛበትና ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ አጋላጭ መሆኑን ጠቅሰው ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ጨብጦ ራሱን እንዲጠብቅ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
ሚኒስቴሩ ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን ይፋ ያደረገው መርሃ ግብር በጤና ጣቢያዎችና መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች የግፊትና ስኳር ምርመራ እና ልየታ የሚያደርጉ የጤና ባለሙያዎች አቅም መገንባት፣ለህክምና የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን በሟማላት አገራዊ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ፖፕሌሽን ሰርቪስ ኢንተርናሽናል (ፒ ኤስ አይ ) የኢትዮጵያ ቢሮ ተጠባባቂ ተወካይ ሩት ወልደትንሳኤ በበኩላቸው፤ ስር የሰደደ የኩላሊት በሽታን በኢትዮጵያ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት መደረጉን ተናግረዋል።
ጥናቱን መሰረት በማድረግም በቀጣይ የሚወሰዱ እርምጃዎች አቅጣጫዎች መቀመጡን አስረድተዋል።
ስር ለሰደደ ኩላሊት በሽታ አጋላጭ የሆኑት ግፊትና ስኳር በሽታዎች ምርመራ የሚያደርጉ ባለሙያዎች አቅም ግንባታ ሥልጠና እንደሚሰጡም አመልክተዋል።
የኩላሊት ጤንነትን ለመጠበቅ የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ህብረተሰቡ የኩላሊት ጤና የሚያስጠብቅበት መንገዶች ላይ በዘመቻ መልክ ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባራት እንደሚከናወኑም አስረድተዋል።
ከሳሃራ በታች ያሉ አፍሪካ አገራት የአስትራዜኒካ ቢሮ ዳይሬክተር አሚት ባክሪ በበኩላቸው፤ አስትራ ዜኒካ "ሄልዚ ሀርት አፍሪካ" በተሰኘ መርሃ ግብር በኩል በአፍሪካ 77 ሚሊዮን አፍሪካዊያን የደም ግፊት ተጋላጭነት ምርመራ ማካሄዱን ተናግረዋል።
ለ11 ሺህ 890 የጤና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
አስትራዜኒካ ሰፊ ልምድ አለው ያሉት ዳይሬክተሩ ስር የሰደደ የኩላሊት በሽታ አስቀድሞ መከላከል ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት በመስራታችን ደስተኞች ነን ብለዋል።