እውቅናው ለበለጠ ድል የሚያነሳሳ ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
እውቅናው ለበለጠ ድል የሚያነሳሳ ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ሕዳር 11/2018(ኢዜአ)፡-የዓለም አትሌቲክስ ለሻምበል አትሌት አበበ ቢቂላ እንዲሁም ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያበረከተው እውቅና እና የዓለም አትሌቲክስ ቅርስ ለበለጠ ድል የሚያነሳሳ መሆኑን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የዓለም አትሌቲክስ ለሻምበል አትሌት አበበ ቢቂላ የ1960 የሮምና 1964 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ድል እንዲሁም ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እውቅና እና የዓለም አትሌቲክስ ቅርስን አበርክቷል።
ሁለቱም እውቅናና የቅርስነት አርማ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በክብር ተቀምጧል።
እውቅናና የቅርስነት አርማውንም የዓለም አትሌቲክስ የቅርስ ዳይሬክተር ክሪስ ተርነር ያስረከቡ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሣ እና አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ተረክበውታል።
የዓለም አትሌቲክስ ለሻምበል አበበ ቢቂላ እና ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሰጠው እውቅና በአትሌቲክስ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ አሻራ ላሳረፉ ታላላቅ ግለሰቦችና ሥፍራዎች የሚሰጠው 'የዓለም አትሌቲክስ የቅርስ ሰሌዳ' (World Athletics Heritage Plaque) ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ አትሌቲክስ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ እንድትታይ ማድረጉን ተናግረዋል።
አትሌት አበበ ቢቂላ የኦሎምፒክ ድል የስፖርት ስኬት ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ትልቅ የኩራትና የነጻነት ምልክት መሆኑንም ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።
ሻምበል አትሌት አበበ ቢቂላ በ1952 የሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ በማሸነፍ አፍሪካንና የጥቁር ሕዝቦችን ያኮራ መሆኑን አስታውሰው፤ በ1956 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ድሉን በመድገም ድንቅ ስኬት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
የእርሱን ፈለግ በመከተልም በርካታ አትሌቶች በዓለም አደባባይ ድል በማድረግ የኢትዮጵያን ዓርማ በክብር ከፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የመዲናዋ ሌላኛው ድምቀት እና በርካታ ሰዎች የሚያሳትፍ መሆኑን ጠቁመው፤ ለሁለቱም እውቅናና ክብር የተሰማቸውን ደስታም ገልጸዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሣ ፤ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዳዲስ አትሌቶችን ከማፍራት ባሻገር ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ዘርፍ የገነባችውን መልካም ዝና ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በማስቀጠል ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመው፣ በተሳታፊ ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚው መሆኑንም ተናግረዋል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለሕዝቦች የአብሮነት እሴት መጎልበት ትልቅ ትርጉም እያበረከተ መሆኑን ጠቁመው፤ እውቅናው ለበለጠ ድል የሚያነሳሳ መሆኑንም አክለዋል።
የዓለም አትሌቲክስ የቅርስ ዳይሬክተር ክሪስ ተርነር፤ የዓለም አትሌቲክስ ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የቅርስነት ሰሌዳ ሽልማትን ሲያበረክት ደስታ ይሰማዋል ብለዋል፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከታላላቅ የአፍሪካ ስፖርታዊ ስኬቶች አንዱ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መስራች ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ለተሰጠው እውቅናና ሽልማት ምስጋናውን አቅርቧል።
ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተሰጠው እውቅናና ክብር በአፍሪካ መጀመሪያው ነውም ተብሏል።