ቀጥታ፡

መድኃኒቶችን በተላመዱ ጀርሞች ምክንያት የሚከሰቱ የጤና እክሎችን ለመከላከል የግሉ ዘርፍ አጋርነት ሊጎለብት ይገባል

አዲስ አበባ፤ሕዳር 11/2018(ኢዜአ)፡-የጸረ ተዋህሲያ መድኃኒቶችን በተላመዱ ጀርሞች ምክንያት የሚከሰቱ የጤና እክሎችን ለመከላከል የግሉ ዘርፍ አጋርነት ሊጎለብት እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ። 

የጤና ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ የፀረ ተዋህሲያን መድሀኒቶች በጀርሞች መላመድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት እና አራተኛውን የአምስት ዓመት ሀገር አቀፍ የትግበራ ዕቅድ ማስጀመሪያ መርሀ ግብርን ባለድርሻ አካላትና አጋር አካላት በተገኙበት በይፋ አስጀምሯል።

የጸረ ተዋህሲያን መድሀኒቶች በበሽታ አምጪ ተህዋሲያን ሳቢያ በሰውና በእንስሳት ጤና ላይ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከልና ለማከም የምንጠቀማቸው መድሀኒቶች ናቸው።


 

ይሁን እንጂ ማህበረሰቡ የጸረ ተዋህሲያን መድሀኒቶችን በአግባቡ ባለመጠቀሙ ጀርሞች የጸረ ተዋህሲያን መድሀኒቶችን በመላመድ አደጋ እያስከተሉ መሆኑ በመርሀ ግብሩ ተገልጿል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት፤ የጸረ ተዋህሲያን መድሀኒቶች በጀርሞች መላመድ ምክንያት በሰዎች ላይ የጤና ቀውስ እየፈጠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በዚህም አምራች የሰው ሀይሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ፤  በሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገትና ምርታማነት  የራሱ የሆነ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የጸረ ተዋህሲያን መድሀኒቶች በጀርሞች መላመድ እያስከተለ ያለውን ችግር ለመፍታት ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር በጀርሞች የተላመዱ ጸረ ተዋህሲያን መድሀኒቶችን በመለየት መፍትሄ ማምጣት የሚያስችሉ በላብራቶሪ የመመርመር አቅምን የማሳደግ ስራ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

የጸረ ተዋህሲያ መድኃኒቶችን በተላመዱ ጀርሞች ምክንያት የሚከሰቱ የጤና እክሎችን ለመከላከል የግሉ ዘርፍ አጋርነት ሊጎለብት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡


 

የዓለም ጤና ድርጅት የኢትየጵያ ተወካይ ዶክተር ቢጆይ ናምቢየር በበኩላቸው፤ የጸረ ተዋህሲያን መድሀኒት በጀርሞች መላመድ በጣም አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የጸረ ተዋህሲያን መድሀኒት በጀርሞች መላመድን ለመግታት እቅድ ነድፋ ወደ ተግባር መግባቷ የሚበረታታ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

በፋኦ የኢትዮጵያ ተወካይ ቸንጀራይ ንጃጉ በበኩላቸው፤ የጸረ ተዋህሲያን መድሀኒት በጀርሞች መላመድ እያሳደረ ያለውን ማነቆ ለመፍታት ኢትዮጵያ የምትደርገውን ጥረት እንደግፋለን ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ በበኩላቸው፤ የጸረ ተዋህሲያን መድሀኒቶች በጀርሞች መላመድ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል ።


 

በዚህም ባለስልጣኑ ጽዱ ኢትዮጵያና ከአየር ብክለት የጸዳች ከተማን ለመፍጠር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

ፅዱ አካባቢን መፍጠር ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር አቅም እንደሚያጎለብት ገልጸዋል።


 

የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጂን ካሴያ፤ የጸረ ተዋህሲያን መድሀኒት በጀርሞች መላመድ እያስከተለ ያለውን ችግር ለመፍታት መሬት የወረደ ስራ መሰራት አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም