ቀጥታ፡

የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የንግዱ ማህበረሰብ እገዛውን ማጎልበት ይጠበቅበታል

‎ሀዋሳ፤ሕዳር 11/2018(ኢዜአ)፡-በሀዋሳ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የንግዱ ማህበረሰብ እገዛውን ማጎልበት እንደሚጠበቅበት የከተማው አስተዳደር  ከንቲባ ጥራቱ በየነ ገለጹ።

ሀዋሳን ለኑሮ፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድና ለቱሪዝም ተመራጭ ከተማ ለማድረግ ግብ ተይዞ  እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ከንቲባው በከተማዋ ከሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር በከተማዋ ነባራዊ ሁኔታና ቀጣይ የልማት ትኩረቶች ላይ ዛሬ መክረዋል።


 

‎በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በሀዋሳ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የንግዱ ማህበረሰብ ድጋፍና እገዛውን ማጎልበት ይጠበቅበታል፡፡

ከተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች አኳያ ከተሞች የሚመሩበት እሳቤ መቀየሩን ያነሱት ከንቲባ ጥራቱ፣ የዜጎችን ህይወት ለሚቀይሩና የኢኮኖሚ እድገትን ማዕከል ላደረጉ ተግባራት ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

በሀዋሳ ከተማ  የለውጥ ሂደት ውስጥ ፍጥነትና ፈጠራን በማከል ከተማዋን ለንግድና ለኢንቨስትመንት እንዲሁም ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

ለዚህም የሀዋሳ ሐይቅና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች፣ የተዘረጉ የመንገድ መሠረተ ልማቶች እንዲሁም እንግዳ ወዳድ ህዝቧ መልካም ዕድሎች መሆናቸውን ነው ከንቲባው ያመላከቱት።

‎በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደርና ሌሎች የልማት ሥራዎችም ለሀዋሳ የተሻለ አቅም እንደሚፈጥሩ አንስተዋል፡፡

ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የከተማ ዕድገት ሁሉንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በመረዳት ግብሩን በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል ማሕበራዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣና ለልማቱም መፋጠን ተሳትፎውን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አባተ ኪሾ በሰጡት አስተያየት፤  እያደገ የመጣውን የህዝብን የልማት ፍላጎት ለማሟላት ግብራችንን በአግባቡ በመክፈል የሚጠበቅብንን እንወጣለን ብለዋል፡፡


 

ከአስተዳደሩ ጎን በመቆም የከተማዋን እድገት ለማፋጠን የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የተናገሩት አቶ ጌቱ ተካ የተባሉ ሌላው የንግዱ ማህበረሰብ አባል ፣ አስተዳደሩ አሰራርን ምቹ ለማድረግ የጀመረውን ስራ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።


 

በውይይት መድረኩ በከተማዋ  የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም