ቀጥታ፡

ለሕብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንተጋለን-  የመንግስት ሠራተኞች 

ደብረ ብርሃን፤ሕዳር 11/2018(ኢዜአ)፡-   ቀልጣፋ አገልግሎት ለሕብረተሰቡ  በመስጠት እርካታን ለማረጋገጥ   በየተሰማሩበት መስክ ተግተው እንደሚሰሩ   የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሠራተኞች ገለጹ።

"አገልጋይና የሰላም ዘብ የመንግስት ሠራተኛ፤ ለሁለንተናዊ እመርታ" በሚል መሪ ሃሳብ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሠራተኞች  ዛሬ ተወያይተዋል።


 

ከውይይቱ ተሳታፊዎች ውስጥ  አቶ ዳዊት አሳምነው በሰጡት አስተያየት፤ በተሰማራንበት የሙያ መስክ ሕብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር ነው ብለዋል።

በተለይ ለሕብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ለመልካም አስተዳደር መስፈን የበለጠ በመትጋት ኃላፊነታቸውን እንወጣለን ሲሉ ገልጸዋል።


 

ለዚህም ብልሹ አሰራሮችንና ሙሰናን በመታገል  ሰላምን ለማፅናት  ለሚደረገው ጥረት  የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

የዛሬው  ውይይት ሠራተኛው  የሕዝብ አገልጋይነትን በመላበስ  መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው  የተናገሩት  ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አሳምነው ወልደትንሳኤ ናቸው።

የስራ ሰዓት ሳይሸራረፍ ተገልጋይን በቅንነት፣ በፍትሃዊነትና በታማኝነት  በማገልገል  እርካታን ለማረጋገጥ በመትጋት  ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡም አክለዋል።


 

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ፤ የመንግስት ሠራተኞች መደበኛ ተግባራቸውን ከማከናወን ባሻገር ለሰላም መከበር ተሳትፏቸውን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።


 

ከዚህ ቀደም ሰራተኛውና ነዋሪዎች በተቀናጀ አግባብ በመስራታቸው ሰላምን ማረጋገጥ  ተችሏል ብለዋል።

አሁን ላይ የተገኘውን ሰላም በማጽናት የአገልግሎት አሰጣጥ መዛነፎችን በማስተካከል የተገልጋዩን  እርካታ ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ዛሬ የተዘጋጀው የውይይት መድረክም የመንግስት ሠራተኞች ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ፈጣንና ውጤታማ አገልግሎት ለሕብረተሰቡ እንዲሰጡ  የሚያግዝ መሆኑንም አስረድተዋል።

በውይይቱ ላይ የከተማ አስተዳደሩ  የተለያዩ  ተቋማት የመንግስት ኃላፊዎችና ሠራተኞች   ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም