የአርሶ አደሩን የአመጋገብ ስርዓት ለማሻሻል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአርሶ አደሩን የአመጋገብ ስርዓት ለማሻሻል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው
አሶሳ፤ ሕዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ የአርሶ አደሩን የአመጋገብ ስርዓት ለማሻሻል የሚያስችል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ከቆላማ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አቡራሞ ወረዳ አምባ 14 ቀበሌ የበለፀገ ምግብ አዘገጃጀት መርሃ ግብር አካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በግብርና ሚኒስቴር የምግብና ስርዓተ ምግብ ጽሕፈት ቤት የምግብና የስርዓተ ምግብ ዴስክ ሃላፊ ያሬድ አዲሱ፤ አርሶ አደሩ ከማምረት በተጨማሪ ምርቱን በመጠቀም የበለፀገ የአመጋገብ ስርዓት እንዲከተል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከቆላማ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የአርሶ አደሩን የአመጋገብ ስርዓት ለማሻሻል የሚያስችል የተቀናጀ የግብርና አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ ጎን ለጎን አርሶ አደሩ በምግብ ስርአት ሂደት ላይ ያለውን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ተናግረዋል።
የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የሥርዓተ ፆታና ሥርዓተ ምግብ አማካሪ አቶ ደመና ለማ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እያከናወነ የሚገኘው የምግብ ስርዓት ተኮር የግብርና ስራ ውጤታማ እንዲሆን የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ የሚያገኘውን ምርት ለምግብነት በማዋል ጤናማ እና አምራች ቤተሰብ እንዲኖረው በየቀበሌው የሚገኙ የግብርና እና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የሚሰጡት ትምህርት ወሳኝነት አለው ሲሉም ተናግረዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ ፍቅሩ አቡን፤ አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ ከሚያገኘው ምርት የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ በተለያዩ የንቅናቄ መድረኮች ላይ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይም በአቡራሞ ወረዳ የተጀመረውን ተሞክሮ በሌሎች አካባቢዎች ለማስፋፋት ቢሮው ከፕሮጀክቱ ጋር በትብብር ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።