በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወሳኝ ድል አስመዘገበ - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወሳኝ ድል አስመዘገበ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 11/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሸገር ከተማን 4 ለ 2 አሸንፏል።
በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ዳግማዊት ሰለሞን በጨዋታ ሁለት በፍጹም ቅጣት ምት አንድ በድምሩ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርታለች።
ሃና ሲሳይ ቀሪዋን ጎል ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመረብ ላይ አሳርፋለች።
ዓይናለም አለማየሁ እና ሰናይ ኡራጎ ለሸገር ከተማ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ21 ነጥብ የሊጉን መሪነት አጠናክሯል።
ሸገር ከተማ በ15 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።
የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ዳግማዊት ሰለሞን በሊጉ ያስቆጠረቻቸውን ጎሎች ብዛት ወደ 14 ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት መሪነቷን አጠናክራለች።
ዛሬ በተደረገ ሌላኛው ጨዋታ ይርጋጨፌ ቡና ባህር ዳር ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል።