በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ የመሰብሰብ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ የመሰብሰብ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል
ደሴ ፤ሕዳር 11/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል በገቢ አሰባሰብ ሂደት ያሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ለልማት የማዋል ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው ከአማራ ክልል ምክር ቤት ጋር በመተባበር በሚሻሻሉ የገቢ አዋጆች ዙሪያ ዛሬ በደሴ ከተማ መክሯል።
በመድረኩ ላይ የቢሮው ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ የሕብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ እየተሰራ ነው።
ለዚህም ከግብር ከፋዩ ማሕበረሰብ ጋር በመወያየት፣ ህገ ወጥ ተግባራትን በመከላከል፣ ገቢ አሰባሰቡን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የክልሉን ገቢ ለማሳደግና ወጪን በራስ አቅም ለመሸፈን ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
የገጠር መሬት መጠቀሚያ ክፍያ፣ የግብርና ሥራዎች ግብር፣ የቴምብር ቀረጥ ክፍያ እና የኤክሳይዝ ታክስን የተመለከቱ አዋጆችን በማሻሻል የገቢ አቅምን ማጠናከርም እንዲሁ።
በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው ውስጥ እስካሁን ድረስ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አውስተው፤ ቀሪውን በቀጣይ ለመሰብሰብ የተጠናከረ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በገቢ አሰባሰብ ሂደት ያሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ለልማት የማዋል ተግባሩም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መንገሻ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
በአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ አሊ ይማም በበኩላቸው፤ ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብር አሰባሰብ ሥርዓት መተግበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለረጅም ጊዜ ሲሰራባቸው የነበሩ አዋጆችን ለማሻሻል፣ አዳዲስ የገቢ አማራጮችን ለማስፋትና ገቢን በፍትሀዊነት ለመሰብሰብ እየተከናወነ ያለው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የደሴ ከተማ ሴት ነጋዴዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እፀገነት ታደሰ ፤ የንግዱ ማሕበረሰብ በሰራው ልክ ግብሩን እንዲከፍል በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት፣ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ አርሶ አደሮችና የሕግ ምሁራን ተሳትፈዋል።