ቀጥታ፡

የዓለም አትሌቲክስ ለሻምበል አትሌት አበበ ቢቂላ እና ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እውቅና እና የክብር ዓርማ አበርክቷል

አዲስ አበባ፤ሕዳር 11/2018(ኢዜአ)፡-የዓለም አትሌቲክስ ለሻምበል አትሌት አበበ ቢቂላ የ1960 የሮምና 1964 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ድል እንዲሁም ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እውቅና እና  የክብር ዓርማ አበርክቷል። 

ሁለቱም እውቅና እና  የክብር ዓርማ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በክብር ተቀምጧል። 


 

እውቅናና የክብር አርማውንም የዓለም አትሌቲክስ የቅርስ ዳይሬክተር ክሪስ ተርነር ያስረከቡ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሣ እና አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ተረክበውታል።


 

የዓለም አትሌቲክስ ለሻምበል አበበ ቢቂላ እና ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሰጠው እውቅና እና ክብር በአትሌቲክስ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ አሻራ ላሳረፉት ታላላቅ ግለሰቦችና ሥፍራዎች የሚሰጠው 'የዓለም አትሌቲክስ የቅርስ ሰሌዳ' (World Athletics Heritage Plaque) ነው። 

አትሌት አበበ ቢቂላ ለኦሎምፒክ ስፖርት ስኬት ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ትልቅ የኩራትና የነጻነት ምልክትም ነው። 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ አትሌቲክስ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ እንድትታይ አድርጓታል ብለዋል። 


 

ሻምበል አትሌት አበበ ቢቂላ በ1960 የሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ በማሸነፍ የአፍሪካንና የጥቁር ሕዝቦችን ያኮራ መሆኑን ጠቁመው፤ በ1964 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ድሉን በመድገም ያስመዘገበው ድንቅ ስኬት ነው ብለዋል። 

የእርሱን ፈለግ በመከተልም በርካታ አትሌቶች የኢትዮጵያን ዓርማ በክብር ከፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። 

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የመዲናዋ ሌላኛው ድምቀት እና በርካቶችን የሚያሳትፍ መሆኑን ገልጸው፤ ለሁለቱም እውቅና እና ክብር የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። 


 

የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሣ በበኩላቸው፤ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዳዲስ አትሌቶችን ከማፍራት ባሻገር ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልጸዋል። እውቅናው ለበለጠ ድል የሚያነሳሳ መሆኑንም ጠቁመዋል። 


 

ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተሰጠው እውቅናና ክብር በአፍሪካ የመጀመሪያው ነውም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም