የማሌዥያ ፌዴሬሽን ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም የኢትዮጵያ ቆይታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ - ኢዜአ አማርኛ
የማሌዥያ ፌዴሬሽን ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም የኢትዮጵያ ቆይታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ
አዲስ አበባ፤ሕዳር 11/2018(ኢዜአ)፡-የማሌዥያ ፌዴሬሽን ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም በኢትዮጵያ የነበራቸውን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩና ልዑካቸው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደማቅ አሸኛኘት አድርገውላቸዋል፡፡
የማሌዥያ ፌዴሬሽን ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር የሁለቱን ሀገራት ሁሉን አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ትብብሮችን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጥልቅ አጋርነት በሚያጠናክሩ በቱሪዝም፣ በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት እና ጤና ዘርፎች የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል፡፡
ከዚህም ባሻገር ስምምነቱ በኳራ ላምፑር ከተማ ምክር ቤትና የአዲስ አበባ አስተዳደር መካከል ትብብር መፍጠር በሚያስችሉ መስኮች ላይም ያተኮረ ነበር፡፡
የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሴሪ አንዋር ኢብራሂም በኢትዮጵያ ቆይታቸው የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጎብኝተዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በተገኙበት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በተካሄደው የኢትዮ-ማሌዥያ ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም ላይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው የኢትዮ-ማሌዥያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደላቀ የኢኮኖሚ ትብብር ለማሸጋገር ወሳኝ ሚና እንዳለውም አረጋግጠዋል፡፡
የሩቅ ምስራቋ እሲያዊት ሀገር ማሌዥያ ፌዴሬሽን ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም የቀናት ኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።