የአፍሪካ ህብረት እና ማሌዥያ የአጋርነት አድማሳቸውን ለማስፋት እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህብረት እና ማሌዥያ የአጋርነት አድማሳቸውን ለማስፋት እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት እና ማሌዥያ በትምህርት እና ዲጂታል ዘርፍ ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር በቅርበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም በአፍሪካ ህብረት ዋና ኮሚሽን ዛሬ ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህብረቱን የጎበኙ የመጀመሪያ ማሌዥያ መሪ ሆነዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ከማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ ሁለቱ ወገኖች በተለያዩ መስኮች ያላቸውን አጋርነት ማጠናከርን ያለመ ነው።
ሊቀመንበሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የአፍሪካ እና ማሌዥያ ትብበር ውስጥ ታሪካዊና የሁለቱን ወገኖች ስትራቴጂካዊ ትብብር እንደሚያጠናክር አመልክተዋል።
እ.አ.አ በ2024 የአፍሪካ እና ማሌዥያ የንግድ ልውወጥ መጠን 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መድረሱን ጠቅሰው፤ ይህም በዘርፉ ያለው ትብብር እየተጠናከረ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ትምህርት የሁለቱ ወገኖች አጋርነት ዋነኛ ምሰሶ መሆኑንና ከእ.አ.አ 2012 አንስቶ ከ40 ሺህ በላይ አፍሪካውያን በማሌዥያ ትምህርታቸውን መከታተላቸውን ገልጸዋል።
ማሌዥያ ቀጣይ የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ሊቀ መንበር መሆኗ እና ብሪክስን ለመቀላቀል ያላት ፍላጎት ኢንቨስትመንትን ጨምሮ ከአፍሪካ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ነው ያሉት።
ሁለቱ ወገኖች በዲጂታል ኢኖቬሽን፣ በግብርና ማቀነባበሪያ ልማት፣ በደቡብ ደቡብ ንግድ እና ትምህርት ዘርፍ ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
ሊቀ መንበሩ የአፍሪካ ህብረት እና ማሌዥያ ዓመታዊ ምክክር እ.አ.አ በ2026 እንዲካሄድ ሀሳብ አቅርበዋል።
የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም በበኩላቸው፤ ማሌዥያ እና አፍሪካ ንግድ፣ ግብርና እና ትምህርትን ጨምሮ በቁልፍ ጉዳዮች ትብብር እያደገ መምጣታቸውን አመልክተዋል።
ሁለቱ ወገኖች ያላቸውን የትብብር አድማስ በማስፋት የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባቸው መግለጻቸውን ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በውይይቱ ላይ የማሌዥያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ተሳትፈዋል።
የአፍሪካ ህብረት እና ማሌዥያ የአጋርነታቸውን አድማስ ለማስፋት እንደሚሰሩ ገልጸዋል::