ቀጥታ፡

ለፈጠራ ስራዎች የተሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት የፈጠራ ስራዎችን ለማበረታታት የሰጠው ትኩረት የልማት ስራዎችን በማገዝ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የተቋማት የስራ ሃላፊዎች ገለፁ።

የኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንት በማስመልከት ትናንት ውይይት ተካሂዷል።


 

በመድረኩ መንግስት፣ የግሉ ዘርፍና ስራ ፈጣሪዎች ተቀናጅተው እንዲሰሩ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በተመለከተ ውይይት ተደርጓል።

ሳምንቱ የዘርፉ ተዋንያን ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ለማበረታታት ያለመ መሆኑም ተገልጿል።

በዚሁ ጊዜ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ፤ መንግስት የኢትዮጵያን የኢንተርፕርነርሺፕ ምኅዳር ለማስፋት በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።


 

ባለፉት ሰባት ዓመታት ሥነ-ምህዳሩን ማስፋት የሚያስችሉ ወሳኝ የአሰራርና የሪፎርም አጀንዎች በመቅረጽ ተግባራዊ ማድረጉን ገልጸዋል።

በዚህም ስራ ፈጣሪዎች ከተለምዷዊ አሰራር ተላቀው ንቁ፣ ችግር ፈቺና የስራ ዕድል ፈጣሪ እንዲሆኑ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶር) መንግስት የቴክኖሎጂ ስነ ምህዳሩን ለማስፋት የፖሊሲ፣ ስትራቴጂና የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባቱን አስታውቀዋል።


 

በዚህም በቅርቡ የጸደቀው የስታርታፕ አዋጅ በዘርፉ ሲያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍና አዳዲስ እድሎችን በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል ነው ያሉት።

የዲጂታል መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት በተደረጉ ጥረቶች የዳታ ቤዝና የኢኖቬሽን ኢንኩቤሽን ማዕከላት መገንባታቸውን ጠቅሰዋል።

በተሰሩት የዲጂታል መሰረተ ልማት ስራዎች በመታገዝ ሀብት ማፍራት የጀመሩ ስታርታፖች እየተበራከቱ መምጣታቸው ለውጤታማነቱ ማሳያ ነው ብለዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሃፅዮን በበኩላቸው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግስት የጀመራቸው የልማት ስራዎች ውጤት ማስገኘታቸውን አስታውቀዋል።


 

በልማት ስራዎች የግል ዘርፉ ሚና እየጨመረ እንዲሄድ እንዲሁም የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት ይሰራል ብለዋል ።

የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት የአካዳሚክ ጉዳዮች ሃላፊ ገነነ አበበ(ዶ/ር) ኢንስቲትዩቱ ለፈጠራና ኢኖቬሽን፣ ችግሮችን ወደ ዕድል ለመቀየርና የማይበገር ሀገራዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

ኢንስቲትዩቱ የተለያየ ክህሎት ያላቸው ዜጎች እውቀታቸውን ወደ ተግባር የሚቀይሩበት ምህዳር በማዘጋጀትና ከፋይናንስ ተቋማት በማገናኘት ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም