በክልሉ ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል የሕዝቡን ሰላምና ደሕንነት የማስጠበቁ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል የሕዝቡን ሰላምና ደሕንነት የማስጠበቁ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል
ጎንደር፤ ሕዳር 11/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከልና የሕግ የበላይነትን በማስጠበቅ የሕዝቡን ሰላምና ደሕንነት የማስጠበቁ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ገለጸ።
ከጎንደር ቀጣና ለተውጣጡ የፖሊስ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የተዘጋጀ የአቅም ግንባታ ስልጠና በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በስልጠናው መድረክ ላይ በክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ ባደረጉት ንግግር ፤ የክልሉ ፖሊስ አመራርና አባላቱ ለክልሉ ሰላምና የሕግ የበላይነት መከበር ዋጋ መክፈላቸውን አስታውሰዋል።
በዚህም ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ጠቁመው፤ ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት አስቀድሞ በመከላከልና የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የሕዝቡን ሰላምና ደሕንነት ማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ተቋሙ በርካታ የሪፎርም ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ ሪፎርሙም ተቋማዊ የአስተሳሰብና የአመለካከት አንድነትን ለማምጣት ወሳኝ እርምጃ ነው ብለዋል።
ሪፎርሙን መሰረት አድርጎ የሚሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠናም በአግባቡ በመከታተል በቀጣይ ሃላፊነታቸውን በላቀ ብቃት እንዲወጡ ለማስቻል የተመቻቸ መሆኑን አስረድተዋል።
በፈጣንና ተለዋዋጭ ዓለም ዘመኑ የሚጠይቀውን ፖሊሳዊ እውቀት መሰረት ያደረገ አደረጃጀትና መዋቅር ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ናቸው፡፡
የፖሊስ አመራርና አባላትን ተግባርና ሀላፊነታቸወን በብቃት እንዲወጡ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወቀ አስፈሬ በበኩላቸው፤ የሕግ የበላይነት በማረጋጋጥ የወንጀል ድርጊቶችን በመቆጣጠር ረገድ የፖሊስ መዋቅሩ ተሳትፎና ትብብር ውጤት እንዲመጣ አግዟል ብለዋል።
በቀጣይ የላቅ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ሪፎርሙን ወደ ተግባር በማሸጋገር የሕዝብን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጎልበት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለአንድ ሳምንት በሚቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ላይ ከጎንደር ከተማ፣ ከማዕከላዊ፣ ከሰሜንና ከምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተውጣጡ ከፍተኛና መካከለኛ የፖሊስ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡