የጅማ ከተማ መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት አሰጣጥ እንግልትን በማስቀረት ጊዜና ገንዘባችንን ቆጥቦልናል - ተገልጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
የጅማ ከተማ መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት አሰጣጥ እንግልትን በማስቀረት ጊዜና ገንዘባችንን ቆጥቦልናል - ተገልጋዮች
ጅማ፤ ህዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ የጅማ ከተማ መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት አሰጣጥ እንግልትን በማስቀረት ጊዜና ገንዘባቸውን እንደቆጠበላቸው የከተማዋ ተገልጋዮች ገለጹ።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ህዝቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ እያነሳቸው የሚገኙ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የተዘረጋ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ነው።
አገልግሎት አሰጣጡን አስመልክተው ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ ተገልጋዮች መካከል አቶ ሞአዝ ጅሀድ በማእከሉ የተገኙት የግብር መለያ ቁጥር ለማውጣት መሆኑን ገልፀው በፍጥነት በመስተናገዳቸው ጊዜ ማትረፋቸውን ተናግረዋል።
የተጀመረውን ቀልጣፋ አገልግሎት በማስቀጠል ተገልጋዮች ከአገልግሎቱ ያተረፉትን ጊዜ በልማት ላይ እንዲያውሉት የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ መረጃን በመፈለግ የሚባክንን ጊዜና የተንዛዛ አሰራርን ያሻሻለ መሆኑን የገለፁት ደግሞ ሌላኛዋ ተገልጋይ ወይዘሮ ኢንዲያ መሀመድ አሚን ናቸው።
ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ረጅም ቀጠሮን ከመስጠት በተጨማሪ አገልግሎቱን በፍጥነት ለማግኘት አዳጋች እንደነበረ አስታውሰው ባገኙት ቀልጣፋ መስተንግዶ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ወይዘሮ ካሚላ ጀማል በበኩላቸው የተጀመረው ዘመናዊና ፈጣን የአገልግሎት አሰጣጥ መጠናከር እንዳለበት ጠቁመው ከመረጃ ዴስክ ሰራተኞች እስከ ባለሙያዎች ያለው ቅንጅታዊ አሰራር የተገልጋዩን እርካታ ማሳደጉን መስክረዋል።
መንጃ ፍቃድ ለማደስ በአገልግሎት ማእከሉ የተገኘው ወጣት አስረስ ዮሀንስ፤ ዘመናዊ አሰራሩ ቀደም ሲል የነበረውን የተዛዛ አገልግሎት አሰጣጥ በእጅጉ የቀየረው በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብሏል።
የጅማ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ምክትል ስራ አስኪያጅ ጀማል ሳሊ እንዳሉት፤ ዘመናዊ አገልግሎቱ በሰለጠኑ ባለሙያዎችና በቴክኖሎጂ ተደግፎ በተሟላ ሁኔታ እየተሰጠ ነው።
የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ በ25 መስሪያ ቤቶች ከ130 በላይ በሚሆኑ የተለያዩ የአገልግሎት አይነቶች በቴክኖሎጂ በማስደገፍ እየተሰጠ መሆኑንም አክለዋል።
ይህም ብልሹ አሰራርን በማስቀረትና የተገልጋዩን የአገልግሎት እርካታ በማሳደግ ረገድ ተጨማሪ አቅም መፍጠሩንም አቶ ጀማል አስረድተዋል።