ቀጥታ፡

በአርባ ምንጭ "የ40/42" ደረጃ መንገድ መገንባት ለቱሪስት እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል - ጎብኚዎች

አርባ ምንጭ፤ ህዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ ወደ አርባምንጭ ደንና አርባዎቹ ምንጮች የሚወስደው የ"40/42" ደረጃ መንገድ መገንባቱ ለቱሪስት እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጎብኚዎች ገለጹ።

የአርባ ምንጭ ከተማ ቱሪዝም መምሪያ በበኩሉ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት ከተማዋን ከጎበኙ ቱሪስቶች ከ86 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገልጿል።

በመንግስት ትኩረት ከተሰጣቸው አምስት የልማት አውታሮች አንዱ በሆነው የቱሪዝም ዘርፍ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው።

ለዚህም ከገበታ ለሃገር እስከ ገበታ ለትውልድ የተሰሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ለዚህ በማሳያነት የሚጠቀሱ ሲሆኑ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማትም ዘርፉን ለማቃቃት ትኩረት ተደርጓል።

በቱሪዝም መስክ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች በሥራ ዕድል ፈጠራና የቱሪስቶችን ቆይታ በማራዘም ከዘርፉ የሚገኝን ገቢ በማሳደግ ረገድም ፋይዳቸው የጎላ ነው።

የቱሪዝም መዳረሻ በሆነችው አርባ ምንጭ ከተማ የተገነበውና እስከ አርባዎቹ ምንጮች የሚያደርሰው የ40/42 የደረጃ መንገድ የቱሪዝም እንቅስቃሴን እያሳለጠ ነው። 

በጠቅላላው 1ሺህ 680 ደረጃዎች ያሉትና የጋሞን ማንነት እና አርባዎቹን ምንጮች መሰረት ተደርጎ ስያሜ የተሰጠው የደረጃው መንገድ በአካቢው ያሉ የቱሪስት መስህቦችን በርቀት እየተመለከቱ ወደ አርባዎቹ ምንጮች የሚጓዙበት መንገድ ነው፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ጎብኚዎችም ወደ አርባ ምንጭ ደንና አርባዎቹ ምንጮች የሚወስደው "የ40/42 ደረጃ መንገድ መገንባት ለቱሪስት እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ነው የገለጹት።

ከጎብኚዎች መካከል አሜሪካዊው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህር ፕሮፈሰር ቶማስ ክሬይን በአርባ ምንጭና አካባቢዋ ቀልብን የሚስቡ በርካታ መስህቦች እንዳሉ አንስተዋል።

"በተለይ በአማራጭነት የተገነባው የደረጃ መንገድ የአካባቢውን የተፈጥሮ ድንቅ ውበት እንድንመለከት ያስቻለና ከዚህ ቀደም በመኪና ይደረግ የነበረን ጉዞ ያስቀረ ነው" ብለዋል፡፡

የደረጃ መንገዱን መጓዝ ለአዕምሮ እርካታ ብቻ ሳይሆን ለሰውነት ጤናም ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ሌላኛዋ ጎብኚ ወይዘሮ ቆንጂት ብዙነህ በበኩላቸው ወደ ቱሪስት መስህቦች የሚወስደው የደረጃ መንገድ ለቱሪስት ምቹ በሆነ ሁኔታ መገንባቱ ለአካባቢው ተጨማሪ መስህብ ነው ብለዋል።

የደረጃ መንገዱ የጫሞና አባያ ሐይቆችን፣ የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ እና የእግዜር ድልድይን በርቀት ሆኖ መመልከት ስለሚያስችል የጎብኚዎችን ትኩረት እንደሚስብ ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ልማት ማህበር ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደጉ ደሳለኝ የደረጃ መንገዱ በልማት ማህበሩ ወጪ እንደተገነባና 1 ሺህ 680 ደረጃዎች እንዳሉት ገልጸዋል።

በጠቅላላው 1 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መንገዱ ወደ አርባዎቹ ምንጮች የሚጓዙ ቱሪስቶችን እንቅስቃሴ የሚያሳልጥና በአርባ ምንጭ ጥቅጥቅ ደን ላይ የሚደርሰውን ሰው ሠራሽ አደጋ የሚታደግ መሆኑን ገልጸዋል።

የአርባ ምንጭ ከተማ ቱሪዝም መምሪያ የቱሪዝም ፕሮሞሽን ባለሙያ ወይዘሪት ታደለች ደጀነ የጋሞ ልማት ማህበር ያስገነባው የ40/42 ደረጃ መንገድ የቱሪስት እንቅስቃሴን እያሳለጠ መሆኑን ተናግረዋል።

አርባዎቹ ምንጮች፣ የአርባ ምንጭ ደንና የአዞ ራንችን ጨምሮ በአካባቢው ያሉ መዳረሻዎች ዋነኛ የቱሪስት መስህቦች መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

መስህቦቹ ባለፉት ሦስት ወራት ከ63 ሺህ 850 በሚበልጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች የተጎበኙ ሲሆን ከዚህም ከ86 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብልዋል።

በተያዘው ዓመት ለአገልግሎት የበቃው "የ40/42" ደረጃ መንገድ መገንባትም ለቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት ምቹ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም