ቀጥታ፡

የማሌዥያ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት የአፍሪካ እና ማሌዢያ ውጤታማ ትብብር ማሳያ ነው - የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ የማሌዥያ እና የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት የአፍሪካ እና ማሌዢያ ውጤታማ ትብብር ማሳያ ነው ሲሉ የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም ጋር ተወያይተዋል።

የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ እና ማሌዢያ የሁለትዮሽ ትብብር እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ማሌዥያውያን ኢትዮጵያ ያላትን ታሪክ በውል እንደሚገነዘቡ ገልጸው ይህም ለሀገራቱ ግንኙነት ልዩ ገጽታ እንደሚሰጠው ተናግረዋል።

ሁለቱ ሀገራት በብሪክስ ማዕቀፍ ያላቸውን ትብብር በማንሳት ማሌዥያ የብሪክስ አጋር ሀገር እንድትሆን ኢትዮጵያ ላደረገችው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የሀገራቱ በደቡብ ደቡብ የትብብር ማዕቀፍ ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸውም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት።


 

በአዲስ አበባ የተካሄደው የኢትዮጵያ እና የማሌዥያ የቢዝነስ ፎረም ለሀገራቱ ትስስር መጠናከር አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ገልጸዋል።

ማሌዥያ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ በባህል እና ሳይንስን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት ብለዋል።

በሌላ በኩል ማሌዥያ አባል የሆነችበት የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ማህበር(ኤስያን) ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ገበያ ያላቸውን ተደራሽነት ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው አመልክተዋል።

የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሀገራት መግቢያ በር መሆኗ ማሌዢያ ከኢትዮጵያ ጋር ትብብሯን ማጠናከሯ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርላት ነው የገለጹት።

የማሌዥያ እና የኢትዮጵያ ትብብር የማሌዢያ እና የአፍሪካ ውጤታማ ትብብር ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም