በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ ያደረገበትን ድል አስመዘገበ - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ ያደረገበትን ድል አስመዘገበ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዳማ ከተማን 4 ለ 0 አሸንፏል።
በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ረድኤት አስረሳኸኝ ሁለት ግቦችን ስታስቆጥር ምርቃት ፈለቀ እና ቅድስት ዘለቀ ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
በውድድር ዓመቱ አምስተኛ ድሉን ያስመዘገበው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ15 ነጥብ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት ደረጃውን ከሶስተኛ ወደ ሁለተኛ ከፍ አድርጓል።
በአንጻሩ በሊጉ አራተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አዳማ ከተማ በሰባት ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።