ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ ለዱር እንስሳት ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግ ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ ህብረተሰቡ ለዱር እንስሳት እና ለብሔራዊ ፓርኮች ተገቢውን ጥበቃ እና እንክብካቤ እንዲያደርግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ገልጿል።

በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ሃብት ባልተቀናጀና አግባብነት በሌለው አጠቃቀም ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነና የአደጋ ተጋላጭነቱ እየጨመረ በመምጣቱ መንግስት ሀብቱን ለመጠበቅ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡

በዱር እንስሳት እና በዱር እንስሳት ውጤት ላይ የሚደረገው ያልተገባ አደን የዱር እንስሳቱን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ተከትሎ ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ማድረግ በማስፈለጉ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን መኮንን ባለስልጣኑ የሚያስተዳድራቸው ብሔራዊ ፓርኮች በአብዛኛው በሰው ሰራሽና በመሰረተ ልማት አለመሟላት የተነሳ በያዟቸው የዱር እንስሳት ሀብቶች ላይ አደጋ መደቀኑን ተናግረዋል።

ይህንኑ መሰረት በማድረግም ህብረተሰቡ የዱር እንስሳትን በተመለከተ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ለዱር እንስሳቱና ለብሔራዊ ፓርኮች ተገቢውን ጥበቃ እና እንክብካቤ እንዲያደርግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በብሄራዊ ፓርኮች አካባቢ የሚስተዋለውን የመሰረተ ልማት ክፍተት ለመሙላት በተለያዩ ኢንሼቲቮች ይፋ ያደረጓቸው ስራዎች ለዘርፉ መነቃቃት መፍጠራቸውን ገልፀዋል።

ለአብነትም በባሌ እና በጨበራ ጩርጭራ ብሄራዊ ፓርኮች የተሰሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን አንስተዋል።

ለዱር እንስሳት ሀብት ተገቢው ጥበቃ እንደሚደረግ ጠቁመው የተገኙትን አበረታች ውጤቶች የሚያስቀጥሉ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።


 

በዚህም የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ከሰው ሰራሽ ተግዳሮት ለማላቀቅ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ከሁለት ሺህ በላይ አባወራዎች ምቹ ወደ ሆነ ቦታ እንዲዛወሩ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በቀጣይም በዱር እንስሳት እና በብሔራዊ ፓርኮች ላይ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

በተለይም በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ የዱር እንስሳት መኖሪያዎችን ከህገ ወጥ ሰዎች ማላቀቅና የደን ጭፍጨፋን መከላከል የሚያስችል ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም