ቀጥታ፡

የባሕር በር ጥያቄ የሀገር ሕልውና እና የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ በመሆኑ የጋራ አጀንዳችን ነው - የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

ሐረር፤ ህዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ የባሕር በር ጥያቄ የሀገር ሕልውና እና የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ በመሆኑ የጋራ አጀንዳችን ነው ሲሉ የተለያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የኢኮኖሚ፣ የብሔራዊ ደሕንነት፣ የቀጣናዊ ልማት ትስስር ብሎም የሀገር ሕልውና ጉዳይ ነው።

ጥያቄው ታሪካዊ፣ ሕጋዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረት ያለው በመሆኑ ምላሽ ይሰጠው ዘንድ የዲፕሎማሲ ጥረቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በሐረሪ ክልልና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የሀገር ሕልውና እና የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ በመሆኑ የጋራ አጀንዳችን ነው ብለዋል።

የድሬዳዋ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ እና የድሬዳዋ ሐረር የኢትዮዽያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) አስተባባሪ ዮናስ በትሩ፤ በመልክአ ምድርም ይሁን በታሪክ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር የተነጠለ ሕይወት ሊኖራት አይችልም ነው ያሉት።

በመሆኑም የኢትዮዽያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከሕልውና ጋር የተያያዘ እንዲሁም እውነታን የያዘ በመሆኑ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር አጥታ በቆየችባቸው ዓመታት ብዙ ዋጋ መክፈሏን ያነሱት አቶ ዮናስ፤ አሁን ላይ የትውልድ ጥያቄ እና የሀገር ሕልውና ጉዳይ ሆኖ መምጣቱን ገልጸው፤ ምላሽ ሊያገኝ ግድ መሆኑን ገልጸዋል።

የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የሀገር ሕልውና እና የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ በመሆኑ ሁላችንንም ይመለከተናል ነው ያሉት።


 

የሐረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢና የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ አስተባባሪ አብዱልሃፊዝ አሕመድ፤ የባሕር በር ጥያቄ የሀገር ሕልውና ጉዳይ በመሆኑ ምላሽ የሚሻ የትውልዱ ጥያቄ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ ፓርቲያቸው ጠንካራ አቋም ያለው መሆኑን አንስተው፤ ለተግባራዊነቱ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

የትውልድ ጥያቄ የሆነውን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሁላችንም ስራ ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም