በተቀናጀ ግብርና በተፈጠረልን የስራ ዕድል ውጤታማ ሆነናል - ኢዜአ አማርኛ
በተቀናጀ ግብርና በተፈጠረልን የስራ ዕድል ውጤታማ ሆነናል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ አንድም መሬት ጦም ማደር የለበትም በሚል መርህ የተጀመረው ኢኒሼቲቭ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በመሰማራታቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የየም ዞን ወጣቶች ገለጹ።
20ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ የሚዲያ ባለሙያዎች በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በየም ዞን የተለያዩ የልማት ስራዎች ምልከታ አድርገዋል።
ጉብኝት ከተደረገባቸው ስፍራዎች መካከል በየም ዞን ዴሪሳጃ ዙሪያ ወረዳ ዲቻ ቀበሌ የተቀናጀ የግብርና ልማት አንዱ ነው።
በተለይ 30:40:30 በሚል የተጀመረው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ኢኒሼቲቭ አሁን ላይ ወደ አትክልትና ፍራፍሬ ክላስተር አድጎ በርካቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ይህ ኢኒሼቲቭ በዞኑ ስራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት ቀደም ሲል ነዋሪዎች የማይኖሩበትን የዴሪሳጃ ዙሪያ ወረዳ ዲቻ ቀበሌ አሁን ላይ ለመኖሪያ ምቹና ለአይን ማራኪ ማድረግ ተችሏል።
እንዲሁም በርካታ ወጣቶች በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡
ወጣት አቤል አሸቱ በየም ዞን ዴሪ ሳጃ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ ሲሆን በ2012 ዓ.ም ከሌሎች ወጣቶች ጋር ተደራጅቶ በግብርና ስራ መሰማራቱን ይናገራል።
በተፈጠረለት የስራ ዕድል በተቀናጀ የግብርና ስራ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በመሰማራት ከራሳቸው አልፈው ለገባያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን ገልጿል።
ምርታቸውን ገበያ ማድረስ የሚያስችላቸውን መሰረተ ልማት ቢዘረጋላቸው የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አንስቷል።
ጥምር ግብርናን እውን ለማድረግ ከአስተሳሰብ መጀመር አለበት የሚለው ሌላኛው ወጣት አለማየሁ ሰቢ በውስን መሬት በአይነት ብዙ ማልማት እንደሚቻል አመላክቷል።
የአትክልትና ፍራፍሬ ምርታቸውን ለአካባቢው ከማቅረብ ባለፈ ለተለያዩ አካባቢዎች እያቀረቡ እንደሚገኙም ተናግሯል።
በተፈጠረላቸው የስራ ዕድል ከእለት የምግብ ፍጆታ ባለፈ ሀብት መፍጠር መጀመራቸውን የገለጸው ደግሞ ወጣት አጥናፍ ወልደየሱስ ነው።
የተቀናጀ ግብርና ለቤተሰብ ብልጽግና በሚል በተጀመረው የአትክልትና ፍራፍሬ ኢኒሼቲቭ የተገኘው ውጤት ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ማሳያ መሆኑንም ነው የተናገረው።
ቀጣይ በዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን ወጣቶቹ ገልጸዋል።