ቀጥታ፡

መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ እና ማሌዥያ ትብብር ብሩህ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ እና ማሌዥያ ትብብር ብሩህ እና ይበልጥ ጠንካራ የሚሆንበት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም ጋር ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ እና ማሌዥያ ታሪካዊ ወዳጅነትና ትብብር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገልጸዋል።


 

የሀገራቱ ግንኙነት በዲፕሎማሲ ትስስርና የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ(ናም) እና የደቡብ ደቡብ ትብብር ባላቸው የጋራ ቁርጠኝነት ላይ የተመሰረተ እንደሆነም ተናግረዋል።

ማሌዥያን በጎበኙበት ወቅት የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም ላደረጉላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበው ሁለቱ መሪዎች በሀገራቱ የሁለትዮሽ ትብብር ላይ ግልጽ የሆነ ውይይት ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

ጉብኝቱ ለሀገራቱ ወዳጅነትና ትብብር አዲስ በር የከፈተ መሆኑን ገልጸው በአዲስ አበባ የተደረገው ውይይትም በተለያዩ መስኮች ያለውን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብር ለማጠናከር ዕድል መፍጠሩን አንስተዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለትዮሽ ውይይቱ ወቅት ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ሊያጎልብቱ በሚችሉባቸው በርካታ ዘርፎች መዳሰሳቸውን ነው ያብራሩት።

የኢትዮጵያ እና ማሌዥያ መጻኢ ጊዜ ብሩህ እና ጠንካራ እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለኝ ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም ወደ ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጡ ያሉ ሲሆን ቀሪ ቆይታቸው ፍሬያማ እንዲሆንም ተመኝተውላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም