ቀጥታ፡

ሆስፒታሉ ያቋቋመው የኦክሲጅን ማምረቻ ማዕከል ከእንግልት ታድጎናል - ተገልጋዮች

ጎንደር፤ ህዳር 11/2018(ኢዜአ)፡- የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ያቋቋመው የኦክሲጅን ማምረቻ ማዕከል  የተሻለ ሕክምና እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ከእንግልት እንደታደጋቸው የሆስፒታሉ ተገልጋዮች ገለጹ፡፡

በወር ከ17 ሺሕ በላይ ሲሊንደር ኦክሲጅን የማምረት አቅም ያለው የማምረቻ ማዕከሉ ከሆስፒታሉ አልፎ ለሌሎች የመንግስትና የግል ጤና ተቋማትም ምርቱን እያቀረበ መሆኑም ተመላክቷል።

በሆስፒታሉ ሲታከሙ ኢዜአ ያነጋገራቸው ወይዘሮ ማሪቱ መሳፍንት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባደረባቸው የሳንባ ሕመም የ24 ሰዓት የኦክሲጅን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በተፈጥሯዊ መንገድ መተንፈስ ባለመቻላቸው ሆስፒታሉ እየሰጣቸው ያለው የተሟላ የኦክሲጅን አገልግሎት ሕይወታቸውን በማቆየት የተሻለ ሕክምና እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል፡፡

ሆስፒታሉ ራሱን ችሎ ኦክሲጅን ማምረት በመቻሉ በአቅርቦት ችግር ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቆ የነበሩ በርካታ ሕሙማንን ከስጋትና እንግልት  መታደግ መቻሉንም ተናግረዋል።

ሌላዋ ተገልጋይ ወይዘሮ አጥቢያነሽ ገብሩ በበኩላቸው፤ ሕመማቸወን መቋቋም ስላቃተኝ  ኦክሲጂን እየወሰድኩ ተጨማሪ ሕክምና እየተደረገልኝ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በሆስፒታሉ የኦክሲጅን አገልግሎት መኖሩ እንግላት ሳይገጥማቸው አገልግሎቱን በማግኘታቸው ለሌላ ሕክምና ዕድል  እንደሰጣቸው አውስተዋል።

የሰው ልጅ ያለ ኦክሲጅን ለሰከንድ ሕይወቱን ማስቀጠል አይችልም ያሉት ወይዘሮ አጥቢያነሽ፤ ሆስፒታሉ አገልግሎቱን በመስጠቱ የበርካታ ሕሙማን ሕይወት ዳግም እንዲቀጥል ያደረገ ነው ብለዋል፡፡


 

የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተወካይ ኃላፊ ደምስ ሙላቱ፤ የኦክሲጅን ማምረቻው ማዕከል መቋቋም በአቅርቦት እጥረት ችግር ይገጥማቸው የነበሩ ሕሙማንን ሕይወት መታደጉን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በወር ከ17 ሺሕ በላይ ሲሊንደር ኦክሲጅን የማምረት አቅም ያለው የማምረቻ ማዕከሉ ከሆስፒታሉ ውጪ ላሉ የመንግስትና የግል የሕክምና ተቋማት ምርቱን እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚሕም ከዚሕ ቀደም ከባሕር ዳርና ከአዲስ አበባ በማስመጣት ይጠቀም የነበረውን የኦክሲጅን ምርት ማስቀረት መቻሉንም አውስተዋል።፡

አሁን ላይ በሆስፒታሉ በኦክሲጅን እጥረት ምክንያት ሕይወቱ ስጋት ላይ የሚወድቅና ለእንግልት የሚዳረግ ታማሚ የለም ብለዋል።

ሆስፒታሉ ለፅኑ ሕሙማን፣ ለቀዶ ሕክምና፣ ለድንገተኛ፣ ለጨቅላ ሕጻናትና ለስትሮክ ታማሚዎች በቂ ኦክሲጅን በማምረት በአካባቢው ቀልጣፋ የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።


 

በኦክሲጅን ማምረቻው በማሽን ቴክኒሺያንነት ተመድበው የሚሰሩት እሱባለው በእውቀት፤ የኦክሲጅን ማምረቻው ባሉት ዘጠኝ ማሽኖች 24 ሰዓት በማምረት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኦክሲጅን ማምረቻው አቅርቦቱን በሲሊንደርና ወደ ሕሙማን አልጋዎች በተዘረጉ የኦክሲጅን ማስተላላፊያ መስመሮች በፍጥነት ተደራሽ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዓመት 400 ሺሕ ለሚጠጉ ታማሚዎች የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ሆስፒታሉ የተመሰረተበትን 100ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በቅርቡ የኦክሲጅን ማምረቻ ማዕከል አስመርቆ ስራ መጀመሩ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም