ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ መመከት የሚያስችል አቅም እየፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ ለመመከት የሚያስችል ጠንካራአቅም በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

ባንኩ የሳይበር ደህንነት ወርን ለሁለተኛ ጊዜ እያከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት አገልግሎቶች ኤክስኪውቲቭ ምክትል ፕሬዝዳንት ኤፍሬም መኩሪያ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል ልማት ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል።

ይህን ተከትሎም ባንኩ የ(2020 - 2025) የመጀመሪያ ምዕራፍ ዲጂታላይዜሽን ስትራቴጂውን በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቆ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ዲጂታል መር ስትራቴጂ (2025-2030) መሸጋገሩን ገልፀዋል።


 

አሁን ላይ ከባንኩ ጠቅላላ ግብይት ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚከናወነው በዲጂታል መንገድ መሆኑን ጠቅሰው፤ የግብይት ስርዓቱን ደህንነት ለማስጠበቅ በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንM አረጋግጠዋል።

አቶ ኤፍሬም አክለውም የሳይበር ደህንነት አስተዳደርን እስከ ምክትል ፕሬዝዳንት ደረጃ በማሳደግ ባንኩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያው የፋይናንስ ተቋም መሆኑን ገልፀዋል።

በተጨማሪም የሳይበር ደህንነት ክፍሎች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤ.አይ) የሚሠራ የዜሮ ትረስት ደህንነት ስትራቴጂ (Al-powered Zero Trust Security Strategy) መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

የሳይበር ጥቃትን መከላከል የአንድ አካል ብቻ ተግባር አለመሆኑን ጠቁመውም፤ የሚመለከታቸው አካላት ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም