ቀጥታ፡

የህዝብ የሰላም ዘብ በመሆን በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት የሚሰራ ጠንካራ የፖሊስ ኃይል የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

ባሕርዳር፤ ሕዳር 11/2018 (ኢዜአ)፡- የህዝብ የሰላም ዘብ በመሆን በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት የሚሰራ ጠንካራ የፖሊስ ኃይል የመገንባት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።

ለዋና ጠቅላይ መምሪያው የፖሊስ አመራሮችና ከፍተኛ መኮንኖች የአቅም ግንባታ ስልጠና በባሕርዳር ከተማ እየሰጠ ነው።

በክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው፤ በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር ወንጀልን በመከላከል፣ ሰላምን በማፅናት፣ የሕግ የበላነትን ለማረጋገጥ በቴክኖሎጅ እውቀት የዳበረ ተቋማዊ አመራር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ሕዝቡ የሰላም ዘብ በመሆን በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት የሚሰራ ጠንካራ የፖሊስ ኃይል የመገንባት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የስልጠናውም ዓላማ የፖሊስ ሪፎርም አተገባበርን አጠናክሮ በማስቀጠል የዘላቂ ሰላም ግንባታና የወንጀል መከላከል ስራን ለማጎልበት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት በተለይም አመራሩ የላቀ የአመራር ጥበብ፣ የቴክኖሎጂ እና የካበተ እውቀት የሚያስፈልገው በመሆኑ በዚሁ ልክ መዘጋጀት የግድ መሆኑን ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው፤ የክልሉ የፀጥታ ኃይል ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ ሰላሙ ፀንቶ እንዲቀጥልና ልማቱ እንዲፋጠን ሌት ተቀን ተግቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም ስልጠናው በየደረጃው ያለው የፖሊስ አመራር በተናበበና በተቀናጀ አግባብ ለተልዕኮው በላቀ ለመወጣት የሚያዘጋጅ በመሆኑ በትኩረት መከታተል እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም